Fana: At a Speed of Life!

የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ አካባቢን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥያቄ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ አካባቢን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥያቄ መቅረቡን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አስታወቁ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ በርካታ የማይዳሰሱ እና የሚዳሰሱ ቅርሶችን አስመዝግባለች።

ከቅርሶቹም መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሠሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የፋሲል ግንብ፣ አክሱም፣ የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ ይገኙበታል።

በተጨማሪ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የአርኪኦሎጂ ስፍራ፣ የኮንሶ መልክዓ ምድር፣ የመስቀል በዓል አከባበር፣ የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት እና የጥምቀት በዓል አከባበር ተካተውበታል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ለኢዜአ እንዳሉት ፥ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሲሆን ፤ አሁን ላይ የላይኛውን የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢን ለማስመዝገብ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል።

የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ “ሆሞ ሃቢሊስ” የተባለው የጥንት የሰው ልጅ ዝሪያ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ጥንታዊ የድንጋይ መሳሪያዎችን የያዘ አካባቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህም የላይኛውን አዋሽ ተፋሰሰ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ጥያቄ መቅረቡን እና ዝርዝር እጩዎች ውስጥ መካተቱን ጠቅሰው ፥ ከዚህ አኳያ አካባቢውን የሚመለከቱ መረጃዎችን የማደራጀት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ድርጅት ጋር በመሆን የአካባቢውን ካርታ ለማዘጋጀት እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

የመልካ ቁንጡሬ ቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስ ሙዚየም ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ተሰማ በበኩላቸው መልካ ቁንጡሬ በላይኛው አዋሽ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ የቅድመ ታሪክ ቦታዎች ስብስብ የያዘ ሙዚየምና የምርምር ስፍራ መሆኑን አብራርተዋል።

አካባቢው ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ፥ የ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ዓመት እድሜ ያላቸው ጥንታዊ ቅርሶች መገኛ ነው፡፡

ላለፉት 52 ዓመታት የጥናትና ምርምር ቦታ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም ነው ያነሱት፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.