Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ድርድር በማድረግ የሀገሪቱን ጥቅም ማስከበር እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዳሴ ግድብና የአባይ ወንዝ ላይ የሚመክር የምሁራን የውይይት መድረክ በዛሬው እለት ተካሄዷል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ በሆነው የህዳሴ ግድብና የአባይ ወንዝ ላይ የመከረውና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ነው የተካሄደው።

መድረኩ ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በመድረኩ ላይ፥ የውይይቱ ዋና ዓላማው በታላቁ የህዳሴ ግድብና አባይ ወንዝ ላይ የሚደረጉ ድርድሮች በእውቀት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ማገዝ ነው ብለዋል።

ከተፈጥሮ የተሰጠንን በረከት በአግባቡ መጠቀም እንዳንችል ለዘመናት ጫና ሲደረግብን ቆይቷል አሁንም እየተደረገብን ይገኛል ያሉት ፕሮፌሰር ሂሩት፥ ይሄንን በእውቀት፣ በዲፕሎማሲ፣ በብልሃትና በጥበብ የአገራችንን ሉዓላዊነትና ጥቅም ለማስከበር በመስራት ማሸነፍ እንችላለንም ነው ያሉት።

በመድረኩ በግድቡ ዙሪያ ያጋጠሙንን ችግሮች በመዳሰስ መፍትሄው ምን መሆን አለበት የሚለውን እናያለን ሲሉም ተናግረዋል።

ግድቡ በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራ እንደመሆኑም ከወንዙ ተፋሰስ ሃገራት ጋር በራስ ወዳድነት ሳይሆን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ድርድር በማድረግ ጥቅማችንን ማስከበር ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመሰል ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመው ውይይቱ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው፥ የህዳሴ ግድብና የአባይ ወንዝ ጉዳይ በሀብትና በእውቀት መተባበር የሚያስፈልግበት ወቅታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ምክክሩ ኢትዮጵያ እውቀትን መሰረት አድርጋ መብቷን እንድታስከብር የሚያግዝ፣ እንዴት መተጋገዝ እንደሚቻል የሚያመላክት፣ ከምሁራን እውቀትና ልምድ መፍትሄ ለማሰባሰብ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

በመድረኩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እና አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ በአባይ ወንዝ ላይ የኢትዮጵያና ግብፅ ግንኙነት ያለውን ታሪካዊ ዳራ አቅርበው ውይይት ተካሄዶበታል።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፥ ግብፅ የአባይ ወንዝ ተፋሰስን የመቆጣጠር የዘመናት ፍላጎት እንዳላትና ግብፅ በቅኝ ገዥዎቿ ታግዛ ይህን የተፈጥሮ ሀብት ሽሚያ እውን ለማድረግ በየዘመኑ መጣሯን አውስተዋል።

የግብፅ ተከራካሪዎች ዛሬም ድረስ የሚያነሱት በ1902 በአጼ ምኒልክ የተፈረመው የኢትዮጵያ እና እንግሊዝ ስምምነት አባይ ወንዝ ላይ ግድብ ከመስራት አይከለክልም የሚለውን ነው ያሉት ፕሮፌሰር ባህሩ፥ በወቅቱ የተፈረመው የድንበር ውል አንቀፅ 3 ኢትዮጵያ ውሀውን ያለ ሱዳን እና እንግሊዝ ፈቃድ መድፈን አትችልም እንደሚልም ጠቁመው ይህ አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ነው ብለዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ተያይዞ የምትቀበለው የ2015 የመርሆዎች ስምምነት ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብፅ ግን ኢትዮጵያን ያገለገሉ ስምምቶችን እና ደንቦችን ታነሳለች፤ የዚህ ዋነኛ ምክንያት የ2015 ስምምት ግብፅን ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ ልዩ መብት አይሰጣትም ሲሉም ነው የተናገሩት።

ይህ ግብፅ ሌላ ስምምነት እንድትፈልግ አድርጓል፤ የግብጽ አቋም በየጊዜው ተለዋጭ መሆኑ ድርድሩን አስቸጋሪ እንዳደረገውም አስታውቀዋል።

ግብፅ በዚህ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር የፈለገችው በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት አለ በሚል ነው፤ ስለዚህ የውስጥ ችግሮችን በውይይት ፈተን ብሔራዊ ጥቅማችን ላይ ማተኮር ይገባናል ብለዋል አምባሳደር ኢብራሂም።

በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በተለያየ ከፍተኛ ሀላፊነት ኢትዮጵያን ያገለገሉት ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ኪዳኔ አለማየሁ በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ግብፅ የግድቡን የውሀ ሙሌት እና አባይን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ እየሰራች በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ድምጻቸውን አጉልተው ማሰማትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ጫና ለማሳደር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሀኑ፥ ግብፅ ዛሬ ድረስ ሁለት መንገድ ትከተላለች ያሉ ሲሆን እነዚህም ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ጉልበት ለመጠቀም ማስፈራሪያ ነው ብለዋል።

ሁለቱም አማራጮች በፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ብቻ ሊታይ ለሚገባው አባይ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአላዛር ታደለ

የምሁራን የምክክር መድረኩ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል

1. ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በምታደርገው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የምንገኝ ምሁራን ከመቼውም ጊዜ በላይ በእውቀትና በሙያ ለመደገፍ ቃል እንገባለን።

2. ሃገራችን ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብና በሌሎች ግድቦች የምትሰራቸውን ስራዎች የላቀ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት እንዲችሉ በጥናትና ምርምር ለመደገፍ እንሰራለን።

3.- መንግስታችን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ የወሰደውን አቋም በእጅጉ እያደነቅን በሃገር ውስጥ እና በዓለም ዙሪያ ያለን ምሁራን የተጀመረውን ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲፈጸም በጋራና በግል ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን።

4. የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋሞቻችን እንዲሁም መላው ማህበረሰብ ለግድቡ ስራ ፍጻሜ ባለን እዉቀት፣ ሙያና ክህሎት መደገፋችን እንደተጠበቀ ሆኖ ሃብት የማፈላለጉን ስራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግተን ለመስራት ቃላችንን እናድሳለን።

5. የአባይ ወንዝ እውነተኛ ባለቤቶች የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ ዜጎች ቢሆኑም እስካሁን ከባለቤትነት ጥቅሙን ላልተቋደስነውና በከፋ ድህነትና “ጨለማ” ውስጥ ለምንኖረው ኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ የጥቅም ተካፋይ እንድንሆን የግብጽና የሱዳን ወንድሞችና እህቶቻችን የሰብአዊነት ድምጻቸውን እንዲያሰሙ እንጠይቃለን።

6. የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች ያላቸውን ልዩነት ወደጎን በመተው መንግስታችን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር የወሰደውን አቋም በመደገፍ የሰጡትን ፈጣን ምላሽና የወሰዱትን አቋም ኢትዮጵያውያን ምንም ያህል በፖለቲካ አቋም ቢለያዩም በሀገራቸው ሉዓላዊነት እንደማይደራደሩ የቆየውን የዘመናት ታሪክ የደገሙበት በመሆኑ ያለንን አድናቆት እየገለጽን ለወደፊቱም ሁሉን አቀፍ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንጠይቃለን።

7. አንዳንድ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚወሰኑ ውሳኔዎች ፍትህና እውነትን ብቻ መሰረት ያደረጉ ሳይሆኑ በሀገራዊ ጥንካሬና የመደራደር አቅም ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ተገንዝበን፤ የሀገራችንን ጥቅምና ክብር በማስቀደም በትናንሽ ልዩነቶች ላይ ሳናተኩር የትውልድን ጥያቄና መብት በጋራ እንድናስከብር ጥሪያችንን እያስተላለፍን መከፋፈልና መለያየት የብሄራዊ ጥቅማችን ዋነኛ አደጋዎች መሆናቸውን ተገንዝበን በየትኛውም ሁናቴ የትኛውም አካል አሉታዊ ሚና ከመጫወት እንዲቆጠብ አደራ እንላለን።

8. በዓለም ዙሪያ ያሉ አጋሮቻችን በተለይም አፍሪካውያን ወንድሞቻችና እህቶቻችን ሃገራችን ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት የመጠቀም መብቷን ለማስከበር በምታደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ለመደገፍ ከጎናችን እንዲቆሙ እየጠየቅን ከዚህ በተፃራሪው መብቷን የሚጋፉ ወገኖችን እንዲያወግዙ ጥሪ እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም በሃገር ውስጥና በውጭ ያለን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ህዝባችንንና ሀገራችንን ከድህነት ለማላቀቅ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል ራሳችንን እንድናዘጋጅ ጥሪ እናስተላለፋለን።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.