Fana: At a Speed of Life!

የምክክር ሂደቱ በሥኬት እንዲጠናቀቅ የንግዱ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያውያን የምክክር ሂደት ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በሥኬት እንዲጠናቀቅ የንግዱ ማኅበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ÷ ባለፉት አምሥት ወራት ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ለምክክር የሚጠቅሙ ግብዓቶችን እየሰበሰበ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያውያን አጀንዳ በመሆኑ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአንድ ሀገር ውስጥ ሠላም ከሌለ የኢኮኖሚም ይሁን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉል በመሆኑ በተለይም የንግዱ ማኅበረሰብ ዋነኛ ተጎጂ ይሆናል ነው ያሉት።

ሀገራዊ ምክክሩ ሰፊና የንግዱን ማህብረሰብ ጨምሮ ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ የሚከናወን ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን ጠቁመው÷ኮሚሽኑ በኢትዮጵያውያን ገንዘብና ጉልበት እንዲሁም እውቀት መመራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የውጭ ተቋማትን የገንዘብ እርዳታ እንደማያማትርና በአዋጅ የተከለከለ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመሆኑም በገንዘብ እጥረት ምክንያት አጀንዳው በውጭ ኃይሎች እንዳይጠመዘዝ የንግዱ ማኅበረሰብ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ኮሚሽኑና የንግዱ ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ ሊካተቱለት የሚገቡ አጀንዳዎችን በተመለከተ በቀጣይ ውይይት እንደሚያደርግ የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን÷በአጀንዳዎቹ ላይ መግባባት ላይ እንደሚደረስም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ለቀጠናው ተምሳሌት እንደሚሆን ጠቁመው÷ የንግዱ ማኅበረሰብ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትሥሥር ተጠቅሞ የምክክርን አስፈላጊነት እንዲያጎላ መጠየቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.