Fana: At a Speed of Life!

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ሀብት 1 ነጥብ 7 ትሪሊየን ብር ደርሷል-ዶ/ር ይናገር ደሴ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ሀብት 1 ነጥብ 7 ትሪሊየን ብር መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ገለጹ፡፡
በ2014 በጀት ዓመት የባንኩ ሴክተር በበርካታ የጤናማነት መለኪያዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡንም ዶክተር ይናገር ደሴ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የ2014 ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ትናንት የተገመገመ ሲሆን÷ በመድረኩ የተሻለ አፈጻጸም ከታየባቸው ሴክተሮች መካከል የባንኩ ዘርፍ አንዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም የባንኩ ዘርፍ በተቀማጭ ሀብት መጠን፣ ብድር በማስመለስ መጣኔና በሌሎች የጤናማነት መለኪያዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ነው የተጠቀሰው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ሃብት 1 ነጥብ 7 ትሪሊየን ብር ደርሷል፡፡
ይህም የ26 ነጥብ 7 በመቶ እድገት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው÷ ባለፈው አንድ ዓመት ባንኮች ብድር የማስመለስ አቅማቸውን በ48 ነጥብ 7 በመቶ ማሳደጋቸውን አብራርተዋል፡፡
ለግሉ ዘርፍ የሚያቀርቡት የብድር ምጣኔም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና ይህም በአጠቃላይ የባንኩ ዘርፍ በተሻለ አፈጻጸም ላይ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡
በሌላ መልኩ የቴሌ ብር ወደ ሥራ መግባትን ተከትሎ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመው÷ ይህም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱ እንዲረጋጋ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ለግሉ ሴክተር የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን በቂ አለመሆን አሁንም በድክመት እንደሚነሳ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የወጪ ንግድን ጨምሮ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን የሚያሻሽሉ ተግባራትን በማከናወን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡
ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እንደገለጹት÷ የፋይናንስ ሴክተሩን ለማሻሻል የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ዘርፉን ከውድቀት ታድገውታል፡፡
ለአብነትም ባለፉት አራት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የባንኮች ቅርንጫፍ ቁጥር በ30 በመቶ ማደጉን ጠቁመው÷ ይህም 82 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች የቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን አንስተዋል፡፡
ነገር ግን ከዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካ መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት አሁንም የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነጻ ማስገባት (ፍራንኮ ቫሉታ) ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን አስታውሰው÷ በዚህም መንግሥት ማግኘት ከሚገባው ገቢ መካከል እስከ 50 ቢሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብ ማጣቱን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም ገንዘብ ከሚፈለገው መጠን በላይ ወደ ገበያው እንዳይገባ በመቆጣጠርና ድህነትን በሚቀንሱ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት በአገር ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.