Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ተወያይተዋል።

በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራው ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጉብኝት በማድረግ ለአባል ሀገራቱ መሪዎች ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ያላትን አቋም በማስረዳት ላይ ይገኛል።

በዚህ መሰረት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዛሬው እለት ዑጋንዳ ገብተዋል።

በዑጋንዳ ቆይታቸውም ከዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተገናኝተው መምከራቸው ነው የተገለፀው።

በውይይታቸው በቀጠናዊ እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የጋራ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች አባይ ወንዝ የሁሉንም ሀገራት እና ህዝብ እኩል ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ መጠቀም ስላለው ፋይዳ ሃሳብ ተለዋውጠዋል፡፡

በዚህም ከናይል ተፋሰስ ጋር በተያዘ ኡጋንዳ ያፀደቀችው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አድንቀዋል፡፡

ይህም በናይል ተፋሰስ ላይ ለመድረስ ለታሰበው ስምምነት አጋዥ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቷ፡፡

ከዚህ ባለፈም በአባይ ተፋሰስ ላይ እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች ስላሉበት ደረጃ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በበኩላቸው የዓባይ ወንዝ ፍትሃዊና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፍትሃዊነት እና በዘላቂነት መጠቀም ያለውን ፋይዳ በተመለከተም አንስተዋል፡፡

እንዲሁም ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ በአባይ ጉዳይ ላይ የሚመክር ጉባዔ መጥራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የትራንስፖርት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የነበራቸውን ትብብር በመግለጽ የሁለቱን ሃገራት የጋራ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ቃል ገብተዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደትም ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋትን ለመመለስ ሁሉም አካላት ቁርጠኛ አቋም እንዲኖራቸው ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የተመራ ከፍተኛ ቡድን በትናንትናው እለትም ኬንያ ናይሮቢ በመገኘት ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያላትን ግልጽ አቋም ለፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ማስረዳቱ ይታወሳል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.