Fana: At a Speed of Life!

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ በ60 ቀናት የተገነቡና ነባር የተለያዩ 57 ፕሮጀክቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ60 ቀናት ተገንብተው የተጠናቀቁና ነባር የተለያዩ 57 ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ÷ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ፣ የከተማና የክፍለ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በክፍለ ከተማው የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ ፕሮጀክቶችም÷ አድዋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የምግባ ማዕከል፣ ፓርኮች፣ የክፍለ ከተማው የአስተዳደር ሕንፃ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት፣ ሰባት ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የአደባባይ ማስዋብ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የዳቦ ፋብሪካና መሸጫ ሱቆች ናቸው፡፡
ዛሬ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል በ459 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የክፍለ ከተማው አስተዳደር ሕንጻ የሚገኝበት ሲሆን÷ ሕንጻው በ2014 ዓ.ም ከተጠናቀቁ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 334 ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር÷ “ዛሬ የምንመርቀውን ጨምሮ በ2014 ዓ.ም ይዘናቸው የነበሩ 334 ፕሮጀክቶች በስኬት ማጠናቀቅ ችለናል” ብለዋል።
አያይዘውም እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ በሕዝቡና በበጎ አድራጊ ባለሃብቶች ትብብር ተጨማሪ ከ300 በላይ ፕሮጀክቶች መሠራትመቻላቸውን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶችን በመገንባት ሂደት ሕዝቡ ከጎደለው እያወጣ በየአካባቢው እያደረገ ያለው ተሳትፎ እየተጠናከረ መምጣቱ በእጅጉ የሚያኮራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“በየአካባቢው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለቅመን የሕዝብ ሃብት ስለሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተን በመሥራት አጠናቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል” ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ሀገር የምትገነባው በጋራ ነው፤ ፕሮጀክቶችን ስንጨርስም የምንጠቀምበት በጋራ በመሆኑ ባለሃብቶች የሚያድጉት ሕዝብ በአግባቡ አገልግሎት ሲያገኝ መሆኑን ተገንዝበው ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.