Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጸጥታና ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ ስኬታማ ስራ መከናወኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ወስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ጸጥታና ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በሰጡት ማብራሪያ÷ ባለፉት ጊዜያት የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት አደጋ ላይ የጣሉና የአገርን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ሙከራዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

ይህም በተለይ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን ተጠቅማ ለመልማት እያደረገች ያለውን ጥረት በተደራጀ መልኩ ለማስተጓጎል ዓላማ ያደረገ ሙከራ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ አኳያ ሰሞኑን የአልሸባብ የሽብር ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ በመግባት ጥቃት የመፈጸም ሙከራ ማድረጉን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ላይ በተወሰደው እርምጃም ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ በርካታ ኃይሎች ከሽብር ቡድኑ ጋር በጋራ ተሰልፈው እንደነበር መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ የሸኔ እና ህወሓት የሽብር ቡድኖችና የሌሎች አገር ዜጎች ከአልሸባብ ጋር በጋራ ተሰልፈው መደምሰሳቸውን ነው የገለጹት፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው÷ ብሔራዊ የጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት አገራዊ የጸጥታና ደህንነት ስጋቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ተግባራትን በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ምክር ቤቱ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ ኮንትሮባንድ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ኢመደበኛ አደረጃጀትና አጠቃላይ የደህንነት ስጋት የሚፈጥሩ ኃይሎች ላይ ህግ የማስከበር ስራ እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጦ ወደ ስራ መግባቱን ነው ያነሱት፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባም ባለፉው አንድ ወር የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ስራ መከናወኑን ገምግሟል ብለዋል፡፡

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በተከናወኑ ስራዎች በየአካባቢው የነበሩ የኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ወደ መስመር የማስገባት ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም የሞከረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት እርምጃ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ተከናንቦ መመለሱን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በተወሰደው እርምጃ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎችን መመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ብርሃኑ በቀለ ምክር ቤቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸው÷ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚሰሩ የሽብር ቡድኖች ላይ በተወሰደው እርምጃ በርካታ የጠላት ኃይሎች ተደምስሰዋል፤ በርካቶቹ ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት፡፡

ህብረተሰቡ የጸጥታ ኃይሉን በማገዝ ረገድ ያደረገውን ተሳትፎ ያደነቁት ሌተናል ጀነራል ብርሃኑ÷ የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ቀሪ ስራዎች ይከናወናሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይም የትምህርት ቤቶች መክፈቻ ጊዜ፣ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት መቃረቡን ተከትሎ የህዝብን ሰላም ለማወክ የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው፡፡

በመሆኑም መንግስት ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ በህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ኃይሎችን ግንዛቤ በመፍጠር የመመለስና አሻፈረኝ በሚሉት ላይ ደግሞ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን መንግሥት የራሱን አደረጃጀት በመፈተሽ እንደሚያጠራም ነው ያስታወቁት፡፡

ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ስብሰባ በቀደሙት ወራት ተለይተው የነበሩ ሀገራዊ የደህንነት ሥጋቶችን መሠረት በማድረግ የተከናወኑ ተግባራትን የገመገመ ሲሆን፥በአገር አቀፍ ደረጃ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.