Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብ ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቅን ከስፍራው ባበሰሩበት ንግግራቸው÷ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ እንዲሁም ለአፍሪካ እና ለዓለም የተሰጠ የተፈጥሮ ፀጋ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ አገራት የኢኮኖሚክ ትስስርን ካፀደቁ ዓመታት ተቆጥሯል ያሉት ጠቅላይ ሚነስትሩ የኢኮኖሚክ ትስስሩ አንዱ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለጎረቤት አገራት መሸጥ ነው ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይሉ ሙሉ ለሙሉ ሲመነጭ ከጎረቤት አገራት ተሻግሮ ሊጠቅም የሚችል እንደሆነም ጠቅላይሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የህዳሴ ግድቡ ሲጠናቀቅ በጋራ የመልማት እና የማደግ እድልንም በሰፊው እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

አያይዘውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያረፈበት አካባቢ ተራራማና አረንጓዴ መሆኑን ገልጸው፥ይህም ለቱሪዝምና ለተለያዩ የመዝናኛ አማራጮች እንዲሁም ለዓሣ እርባታ እንደሚውል አመላክተዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የዓለም ሕዝብ መጥቶ ለመዝናናት የሚያስችለው ትልቅ ስጦታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የዓለም ሕዝቦች አስፈላጊ ነው ብለው በሚያምኑበት በማንኛውም ጊዜ በዚህ ሥፍራ መጥተው ሊዝናኑ ፣ ሊያዩ፣ ጊዜአቸውን በደስታ ሊያሳልፉ የሚያስችል ከፍተኛ ብቃት እንዳለውም ነው ያስረዱት፡፡

በግድቡ ምክንያት 70 ገደማ ደሴቶች እንደሚፈጠሩ ገልጸው፥ከ40 በላይ ደሴቶች እያንዳንዳቸው ከ10 ሔክታር በላይ ቦታ እንደሚይዙን እና አንዳንዶቹ ከ800 እስከ ከ2 ሺህ ሔክታር በላይ እንደሚሸፍኑም ጠቀመዋል።

ዝቅተኛው ደሴት 5 ሔክታር የሚይዝ ነው ብለዋል፡፡

ደሴቶቹ ከፍተኛ የመዝናኛ ሥፍራና በውኃ ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ሊያስተናግዱ እንደሚችሉና ከፍተኛ የሆነ የዓሣ ምርት ማምረት እንደሚያስችሉም ነው የጠቀሱት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.