Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ሃይማኖት፣ የኢኮኖሚ ደረጃ፣ የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድበን ከፍተኛ ዋጋ የከፈልንበት በዓለም አደባባይ በፅናት የቆምንበት ታላቁ ህዳሴ ግድብ 3ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በድል በማጠናቀቃችን እንኳን ደስ አለን ብለዋል፡፡

ከተባበርን እንችላለን፤ ከተሳሰብን ይከናወንልናል፤ ከተደጋገፍን የብልፅግናን አቀበት በደስታ እንወጣዋለን ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው÷ግድቡ የአይቻልምን መንፈስን በይቻላል የቀየርንበት፤ የትብብራችንና የአንድነታችን መገለጫ ፣ብሄራዊ ኩራታችን፣እና የገጽታችን መለውጥ ማሳያ ጭምር መሆኑን በመጠቆም ለመላው ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ከዘመናት በፊት ያለፈው ትውልድ ዛሬ የምንኮራባቸውን የአክሱም፣ የጎንደርና የላሊበላ ስልጣኔዎች አውርሰውን አልፈዋል፤የታላቁ ህዳሴ ግድብም የዚህ ዘመን ትውልድ የጋራ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ታላቅ የልማት ተቋም ነውም ነው ያሉት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ÷የታላቁ ሕዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የሕዳሴ ግድቡ ለዚህ ስኬት መብቃት የአንድነታችንና የመተባበራችን ውጤት መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷በጋራ ስንቆም ችግሮቻችንን አቅም እያሳጣን የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ እንችላለን ብለዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ÷የኢትዮጵያዊነታችን አርማ የጋራ ጥረታችን አሻራ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ለተጠናቀቀበት ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሰን ብለዋል።

በመልዕክታቸውም ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና የጀመረችውን ጉዞ ትቀጥላለች ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.