Fana: At a Speed of Life!

በምርጫ ሂደት የሚነሱ አለመግባባቶችና ክርክሮች አፈታት ላይ ለፌደራልና ለክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምርጫ ሂደት የሚነሱ አለመግባባቶችና ክርክሮች አፈታት ላይ ለፌደራልና ለክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠና መሰጠቱን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

በስልጠናው ላይ የተገኙት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ስልጠናውን በንግግር ከፍተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራር አባል ዶክተር ጌታሁን ካሳ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና፣ የምርጫ እና የስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/11ን አስመልክተው ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል።

የኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኢሌክቶራል ሲስተምስ ካንትሪ ዳይሬክተር ራኬብ አባተ በበኩላቸው፥ የምርጫ ዑደትን እና አለምአቀፍ መመዘኛዎችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የምርጫ ዑደት እና አለምአቀፍ መመዘኛዎችን እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1162/11 ላይ በተሳታፊዎች የቡድን ውይይት ተደርጓል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውም ይታወሳል።

ውይይቱ በምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ይዘትና አፈጻጸም፣ ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ በሚችሉ ጉዳዮች ዓይነትና ባህሪያት፣ የምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ስለሚደራጁበት አግባብ እና የዳኞች ስልጠና ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.