Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሳርቤት – ጎፋ ማዞርያ – የፑሽኪን -ጎተራ  ማሳለጫ ዘመናዊ የመንገድ ፕሮጀክትን መረቁ 

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሳርቤት – ጎፋ ማዞርያ – የፑሽኪን -ጎተራ  ማሳለጫ ዘመናዊ የመንገድ ፕሮጀክትን ዛሬ መርቀዋል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ÷ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ እና የቻይና ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሺን ኪንግማን እንዲሁም  የመዲናዋ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷንና ስሟን የሚመጥን ውበት ለማላበስ ሰፊ ፕሮጀክቶችን አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የፑሽኪን- ጎተራ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በውበትም ሆነ በጥራት እስካሁን ከተገነቡት የላቀና የከተማዋን ቀጣይ ትልም የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጀመርን እንጂ አልቋጨንም፤ተንደረደርን እንጂ ሩጫችንን አልጨረስንም ያሉት ከንቲባዋ÷  በሠራነው ሳንዘናጋ እና በተራ ኋላ ቀር ጎታች አስተሳሰቦች ጉልበታችን ሳይዝል ለከተማችን ለውጥ መትጋታችን ቋሚ መመሪያችን ይሆናል ብለዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች የከተማዋ ነዋሪዎችም የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡

ግንባታው በ2012 ዓ.ም የተጀመረው ፕሮጀክት 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና ከ30 እስከ 45 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡

ፕሮጀክቱ ፈጣን የአውቶብስ መንገድን ጨምሮ በአንድ ጊዜ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ሊያስተናግድ የሚያስችል፣ 320 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ እና ከመሬት ከፍ ብሎ የተገነባ ረጅም መሳለጫ ድልድይ ያካተተ ነው፡፡

ከቂርቆስ፣ ከጎተራ፣ ከጎፋ ፣ ከሳር ቤት ፣ ከሜክሲኮ እና ከቄራ የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን ከማሳለጡ ባለፈ ለከተማዋ የተለየ ገፅታ ያላበሰ መንገድ መሆኑ ተገለጿል።

ከአሌክሳንደር -ፑሽኪን አደባባይ እስከ ጎተራ ማሳለጫ ድረስ የተገነባው መንገድ÷ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት ከቻይና መንግሥት በተገኘ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብድር የተገነባ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጥራት ደረጃ የተከናወነ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ከመንገድ ፕሮጀክቱ ምረቃ ስነ ስርዓቱ በኋላ÷ አረንጓዴ ዐሻራ የማሳረፍ ስነ ስርዓት ተከናውኗል፡፡

በቅድስት ተስፋዬ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.