Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በዛፖሮዥ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ስትል ከሰሰች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ በዛፖሮዥ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደኅንነትን ጉዳይ ላይ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር መክረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ከጉቴሬዝ ጋር በሥልክ በነበራቸው ውይይት ያነሱት ዩክሬን ጣቢያው ላይ ጥቃት መፈጸሟ ሩሲያ ላይ ትልቅ ሥጋት ፈጥሯል የሚል ነው፡፡

በኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ በመድፍ እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች የታገዘ ጥቃት ተፈጽሟል ስትልም ነው ሩሲያ በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል ስሞታ ያቀረበችው፡፡

ዩክሬን እና ምዕራባውያን ደጋፊዎቿ ደግሞ ሩሲያ ራሷ በምታስተዳድረው ቦታ ላይ ጥቃት እያደረሰች ዩክሬንን ትከሳለች በሚል ወቅሰዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት በጉዳዩ ላይ ከዩክሬን ጎን የተሰለፉ ሲሆን የሩሲያ ወታደራዊ ኃይልም ቦታውን ለቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው ÷ በጣቢያው አቅራቢያ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ኃይል መኖር የለበትም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአካባቢው ነጻ ቀጣና እንዲቋቋም ጥሪ ማቅረባቸውን አር ቲ ዘግቧል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ÷ የዩክሬን ታጣቂዎች ከኪየቭ በሚተላለፍላቸው ትዕዛዝ በኒውክሌር ጣቢያው ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ይሁን እንጅ የአውሮፓ ኅብረት ጥቃቱን ያደረሰችው ሩሲያ ናት የሚለው ዩክሬን በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ እንዳትከሰስ እና በፈጸመችው ጥቃትና ባደረሰችው ጉዳት እንዳትጠየቅ ነው ሲሉ የህብረቱን አቋም ኮንነዋል፡፡

የዛፖሮዥ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኝ በአውሮፓ ትልቁ ለኤሌክትሪካ ኃይል ማመንጫነት የሚውል በሩሲያ የሚተዳደር ጣቢያ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.