Fana: At a Speed of Life!

የሥራና ክህሎት ዘርፍ የሁሉንም ተሳትፎ ይፈልጋል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ እና ክህሎት ዘርፍ በርካታ እድሎች እና ተግዳሮቶች ያሉት፣ የሁሉንም አካላት ተሳትፎና እንቅስቃሴ የሚጠይቅ መስክ ነው ሲሉ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር “ዘላቂ ሥራ ለብሩህ ነገ“ በሚል መሪ ሀሳብ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሁለተኛውን ሀገራዊ የስራ ጉባኤ እያካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው በ2014 በጀት ዓመት 2 ሺህ 58 የአንድ ማዕከል አገልግሎት በየደረጃ ለመለየት ታቅዶ 1 ሺህ 847ቱ ማዕከላት በደረጃ የተለዩ ሲሆን÷ በዛሬው ዕለት እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡

እንዲሁም ውጤታማ ስራ የሰሩ በእነዚህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችም እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በሌላ በኩል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከወራት በፊት ባቀረበው ግልፅ የውድድር ጥሪ መሠረት የ3 ደቂቃ ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) በመላክ ከ260 በላይ የንግድ ሥራ ሃሳቦችን ተቀብሎ የመለየት ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አሸናፊ ሆነው የተለዩት ሦስቱ በመድረኩ እውቅና እና ሽልማት አግኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት÷ መርሐ ግብሩ የላቁ የዘርፉ ፈጻሚዎች ለሌሎች የሞራል ስንቅ የሚሆኑበት ነው፡፡

በሂደቱ አልፋችሁ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግባችሁ ከብዙ አካላት መካከል የላቃችሁ ሆናችሁ የተገኛችሁትን ለማክበር ÷የእናንተ ትጋት የሌላው ተምሳሌት እንዲሆን ለማስቻል ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል፡፡

ዘርፉ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ የጎንዮሽ እና የተዋረድ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ የጀመርንበት አመት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አዳዲስና ተጨማሪ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መደላድል የተፈጠረበት አመት እንደነበርም አመላክተዋል።

በሻምበል ምህረት እና ፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.