Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ  ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር “ዘላቂ ሥራ ለብሩህ ነገ“ በሚል መሪ ሀሳብ  ሁለተኛውን ሀገራዊ የስራ ጉባኤ አካሂዷል፡፡

በጉባኤው የአንድ ማዕከል አገልግሎት በደረጃ በመለየት፤ ውጤታማ  ስራ የሰሩ በእነዚህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እንዲሁም የንግድ ሥራ ሃሳቦችን ላቀረቡ አካላት እና ግለሰቦች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በመድረኩ ተገኝተው የስራ ስምሪት የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን÷ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሰሩ ስራዎች መካከል  የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን መቅረፍና የስራ ዕድል ፈጠራ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሚኒስቴሩን እንደ አዲስ በማቋቋም ወደ ተግባር መገባቱን አንስተው በዚህም የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህም ብዙ ስራ አጥ ወጣቶች ባሉባት ሃገር ይህ ገና ጅምር ነው፤ በሁሉም ባለቤትነት ሰፊ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡

በራሱ የሚተማመን፣ ሃገሩን የሚወድ፣ በሀገሩ ያለውን ፀጋ ፈትሾ ለለውጥ የሚያውል ትውልድ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር አቅም የሚያሳጡ፣ ጊዜያችንን የሚያባክኑ፣ሃገራችንን የሚያስደፍሩ ስምሪቶች የትም አያደርሱም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የትውልዱን ስራ መፍጠር አቅም ማሳደግ፣ የመለወጥ አቅሙን ያሟላ ዜጋ ማብቃት፣ የስራ ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮችን ማስፋፋት እና ማሳደግ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ደመቀ በዚህ መነሻነት ጉባኤው በየዓመቱ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው በኢትዮጵያ ደረጃ ተጠንስሶ ተሻግሮ ደግሞ የአፍሪካ ጉባኤ እንዲሆን ይጠበቃል ነው ያሉት፤ እንዲሆንም ታልሞ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ፡፡

 

በፌቨን ቢሻው

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.