Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን መካለል ለዘመናት ለቆየው ማነቆ ዘላቂ መፍትሔ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን መካለል ለዘመናት ለቆየው ማነቆ ዘላቂ መፍትሔ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፥ በሁለቱም ወገኖች መካከል የተደረገው የአስተዳደር ወሰን ማካለል ሥራ የነበረውን ማነቆ በዘላቂነት የሚፈታና በሌሎች አካባቢዎችም ለሚነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ሥራ ነው ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የተደረገው የአስተዳደር ወሰን የማካለል ሥራ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የወሰን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አካል መሆኑንም ገልጿል።
በየትኛውም እርከን ባለው አስተዳደራዊ አደራጃጀት መካከል ወሰን አስፈላጊ ቢሆንም በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል አስተዳደራዊ ወሰን ባመካለሉ ምክንያት በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ እንግልትና በደል ሲደርስ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
ለአብነትም በአዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ የልዩ ዞኑም ሆነ የአዲስ አባባ ነዋሪዎች የሚገባቸውን የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት አለመቻላቸውን አንስቷል፡፡
ውሳኔው ሕገ ወጥነትን ለመከላከል፣ የሕግ የበላይነትን በጋራ ለማስፈን እንዲሁም ለጋራ ልማትና እድገት ዘላቂ መፍትሔ በመሆኑ ሁሉም አካላት ለተግባራዊነቱ እንዲተባበሩ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል ነው ያለው አገልግሎቱ በመግለጫው፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን መካለል ለዘመናት ለቆየው ማነቆ ዘላቂ መፍትሔ ነው!

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል ግልፅ የሆነ የአስተዳደር ወሰን ሳይካለል ቆይቷል፡፡ በየትኛውም እርከን ባለው አስተዳደራዊ አደራጃጀት መካከል ወሰን አስፈላጊ ቢሆንም በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል አስተዳደራዊ ወሰን ባለመካለሉ ምክንያት በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ እንግልትና በደል ሲደርስ ቆይቷል፡፡ ለአብነትም በአዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ የልዩ ዞኑም ሆነ የአዲስ አባባ ነዋሪዎች  የሚገባቸውን የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት አልቻሉም፡፡

የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ለህዝቡ  ወሳኝ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመስራት ከፍተኛ መስተጓጎልና መጓተት ብሎም መቋረጥ አጋጥሟል። በአዲስ አበባ አፍንጫ ስር ሆነው የልዩ ዞኑ ነዋሪ ልጆች የአንደኛና ሁለተኛ ትምህርት ቤትን ለመፈለግ 40 እና 50 ኪሎ ሜትር ርቆ ለመሄድ ተገደዋል፡፡ ሌሎች መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘትም እንደዚሁ፡፡

ከሁሉም በላይ የመሬት ወረራን ጨምሮ ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ተጠያቂነትን ለማስፈን አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፤ ነዋሪዎች ያለ አግባብ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ተዳርጓል፡፡ ከዚህም አልፎ ችግሩ ለፖለቲካ ቀውስም ዳርጎናል፡፡ ከተማ አስተዳደሩና ልዩ ዞኑ ተቀናጅተውና ተደጋግፈው በጋራ  እንዳያድጉና እንዳይለሙ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በአስተዳደር ወሰን አለመካለል  ምክንያት አሁንም ድረስ በሁለቱም በኩል ህዝቡ በወሳኝ አገልግሎት እጦት፣ ተገቢው መሰረተ ልማት ባለመዘርጋትና በሕገ ወጥ ተግባራት መንሰራፋት ምክንያት ሕዝቡ ለችግር ተጋልጧል፡፡ በአካባቢዎቹም ተደጋገሚ ግጭቶችና የደህንነት ስጋቶች አጋጥማዋል፡፡

በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል መኖር የሚገባው አስተዳደራዊ ወሰን ባለመኖሩ የሕዝብ ጥያቄም ሆኖ ቆይቷል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ዞኑና ከተማ አስተዳደሩ በተናጠልና በጋራ ጥናቶቹን በማካሄድና ኮሚቴዎችን በማዋቀር ያደረጓቸው ሙከራዎች መፍትሔ ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ይህ በመሆኑም በሁለቱም አካባቢዎች በሚኖረው ሕብረተሰብ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ስለሆነም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  የአስተዳደር ወሰን ጉዳዩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ከከተማ አስተዳደሩና ከልዩ ዞኑ የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰፋ ያለ ጥናት በማድረግ የአስተዳደር ወሰን የማካለል ሥራው የፌዴራል መንግስትና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ሕገ-መንግስት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተርን መሰረት በማድረግ የሁለቱን አካባቢዎች የጋራ ተጠቀሚነትና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ በሚያስችል ሆኔታ የማካለሉ ስራ ተከናውኗል፡፡  በሁለቱም አስተዳደር አመራር አካላት መካከልም ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር መካከል ስምምነት ተፈጽሟል፡፡ የሁለቱም አካባቢ ነዋሪዎችም በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ሥራው በሚከናወንበት ወቅት የፌዴራል መንግስትም የቅርብ ክትትል በማድረግ ጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ሰርቷል፡፡

በዚህ መሰረት የአስተዳደር ወሰኑ ሲካለል የከተማ አስተዳደሩንና የልዩ ዞኑን ህዝቦች በጋራ አብሮ መልማትን  መሰረት ያደረገ፣ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር እንዲያጠናክር ታሳቢ ያደረገ፣ የአስተዳደር ወሰን ጉዳዩ ወቅታዊ ሳይሆን ዘላቂና የረጅም ጊዜ መፍትሄ እንዲሆንና ለዘመናት ይደርስ የነበረውን በደልና ጉዳት በሚያስወግድ መልኩ ተጠናቋል፡፡ በመሆኑም የአስተዳደር ወሰኑ መሬት ላይ ወርዶ በሁለቱም በኩል መደበኛ ስራ እስኪጀመር፥  ቀድሞ የነበረው መደበኛ የአገልግሎት አሰጣጡና የፀጥታ ማስከበር ስራዎች ሳይስተጓጓሉ ይቀጥላሉ፡፡ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችም በተያዘው መንገድ የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታም ሳይስተጓጎል ይቀጥላል፡፡ ውሳኔው ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል፣ የሕግ የበላይነትን በጋራ ለማስፈን እንዲሁም ለጋራ ልማትና እድገት ዘላቂ መፍትሔ በመሆኑ ሁሉም አካላት ለተግባራዊነቱ እንዲተባበሩ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የተደረገው የአስተዳደር ወሰን የማካለል ሥራ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የወሰን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አካል ሲሆን፥ በሁለቱም ወገኖች መካከል የተደረገው የአስተዳደር ወሰን ማካለል ሥራ የነበረውን ማነቆ በዘላቂነት የሚፈታና በሌሎች አካባቢዎችም ለሚነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ሥራ ነው፡፡

 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.