Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል እና ዩ ኤን ዲ ፒ በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) በጋራ ለመሥራት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን፥ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ቶሎሳ ገደፋ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሃን ሳለህ ናቸው የተፈራረሙት፡፡

የሥራ ስምምነቱ በቀጣይ አራት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፥ ስምምነቱ በልማትና በሰላም ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ነው።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ ከለውጡ በኋላ በሁሉም መስኮች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡

ስምምነቱ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል፣ የፍትሕና ጸጥታ ተቋማትን የማስፈጸም አቅም ከማጠናከር፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ዓይነተኛ ጥቅም አለው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ የክልሉን የልማት ሥራዎች ለማሳካት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀው፥ በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍም እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶሎሳ እንደገለጹት፥ ለስምምነቱ መተግበሪያ የሚያገለግለው የገንዘብ ድጋፍ የሥራ ዕቅዱን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ይመደባል፡፡

ቱርሃን ሳላህ በበኩላቸው ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፥ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችም እገዛ ማድረጉን ነው ያብራሩት።

የክልሉ መንግሥት የሚተገብራቸውን የልማትና የሰላም ሥራዎች እንደሚያግዙም አረጋግጠዋል፡፡

በክልሉ መንግሥትና በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ትብብር በርካታ የልማት ሥራዎች እየተተገበሩ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

ክልሉ በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የተጠቀሱ የልማትና የሰላም ሥራዎችን ለመተግበር እንዲያግዘው ስድስት ተሽከርካሪዎች ተበርክቶለታል፡፡

በያዴሳ ጌታቸው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.