Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል ተፈራረሙ

 

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 11 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ሽብርተኝነትን፣ የታጣቂዎችን እንቅስቃሴና የተደራጁ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የደቡብ ሱዳን የውስጥ ደኅንነት ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል አኮር ኮር ኩክ ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት በድንበር አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታን ለማደፍረስና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ለማተራመስ ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ፣ አማጺ ኃይሎች፣ ታጣቂ ቡድኖችና የተደራጁ ወንጀለኞችን በጋራ ለመቆጣጠርና እርምጃ ለመውሰድ ሀገራቱ በጋራ የሚሠሩ ይሆናል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን፣ በድንበር አካባቢ የሚካሄዱ የተደራጁ ወንጀሎችን፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ እና የዕጽ ዝውውሮችን፣ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ተቀናጀተው ለመከላከል እንደሚሩ ተመላክቷል፡፡

የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ስትራቴጂክ አጋርነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር በሁለቱም ሀገራት፣ በአፍሪካ ቀንድና በአፍሪካ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የደኅንነት ጉዳዮችን የተመለከቱ ወቅታዊ ለውጦች ሲኖሩ መረጃዎችን እንዲለዋወጡና እንዲጋሩ የሚያስችል መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የላከው መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘዘም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከደቡብ ሱዳን የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር የሲቪል፣ የዜግነት፣ ፓስፖርትና ኢሚግሬሽን ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ጋር ተባብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱ የሀገራቱ ዜጎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሰላማዊና ነጻነቱ የተረጋገጠበት እንዲሆን ተባብረውና ተቀናጀተው ለመስራት ያለመ ነው፡፡

በተለይ በድንበርም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲከናወኑ ስምምነቱ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው መረጃው ጠቁሟል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.