Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ድጎማን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የነዳጅ ድጎማን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል እና የመሠረተ ልማት ደህንነት ላይ በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ የነዳጅ ድጎማን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት መሠረተ ልማት ደህንነት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በስምምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር  ዳግማዊት ሞገስ ባደረጉት ንግግር÷  አገልግሎቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማከናወንን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በመንገድ ደህንነት፣ በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር ደህንነት፣ በአቪዬሸን ዘርፍ ከክልል የፖሊስ መዋቅሮች ጋር በመሆን ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ስምምነቱ የነዳጅ ድጎማ በተቀመጠለት ታሪፍ መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን እና የፌዴራል ፖሊስ ባሉት አደረጃጀቶች በመታገዝ ቁጥጥርና ድጋፍ የሚያደርግበትን እድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው÷ የፖሊስ ኮሚሽኑ ዋነኛ ስራ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሀገርን ሃብት ከጉዳት መጠበቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ስምምነቱ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ እንደሚያግዝ ገልጸው÷ የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ሀገርንም ህዝብንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.