Fana: At a Speed of Life!

የጤና አገልግሎት ሽፋን ፍትሃዊ ተደራሽ እንዲሆን እየተሠራ ነው – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርብቶ አደር አካባቢዎችና ዝቅተኛ አፈጻጸም ባላቸው ዞኖች የጤና አገልግሎት ሽፋን ፍትሃዊ ተደራሽነት እና አጠቃቀም ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጤና ሚኒስቴር እና የዓለም ጤና ድርጅት “በተቀናጀ ጥረት የተፋጠነ የጤና ፍትሃዊነት ለጤናማ እና ፍትሐዊ ማህበረሰብ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ብሔራዊ የጤና ፍትሃዊነት ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ በመጀመሪያው የጤና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አርብቶ አደር እና ዝቅተኛ አፈጻጸም ባላቸው ዞኖች የአምስት ዓመት የጤና ፍትሃዊነት የትግበራ እቅድ በመተግበሩ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በሁለተኛው የጤና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከጂኦግራፊያዊ ልዩነቶች በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶችን በማካተት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የአምስት ዓመት ብሔራዊ የጤና ፍትሃዊነት ስትራቴጂ እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በፆታ፣ በዕድሜ፣በሀብት መጠን፣በትምህርት ደረጃ ፣በጂኦግራፊ እና ልዩ ፍላጎት ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያለውን ኢ-ፍትሃዊነት ለማጥበብ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች ሽፋን እና አጠቃቀም ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለድርሻ አካላት ኢ-ፍትሐዊነትን ለማጥበብና ፍትሃዊነት በማረጋገጥ በጤናው ዘርፍ የተያዙ ግቦችን በማሳካት የዜጎች ብልጽግና እንዲረጋገጥ እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው÷ በሁሉም ዘርፍ የማህበረሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡
ብሔራዊ የጤና ፍትሐዊነት በሁሉም ዘርፍ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኢ-ፍትሐዊነት ለማጥበብ በተለይም የጤና አገልግሎት ሽፋን እና ጥራቱን ለማሻሻል የሚያግዝ ስትራቴጅ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.