Fana: At a Speed of Life!

ትኩረታችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና ላይ ማድረግ አለብን – የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝባችንን ጠላቶች በጋራ በመመከት ትኩረታችንን ሁሉ በሁለንተናዊ ብልጽግና ላይ በማድረግ መረባረብ ይኖርብናል ሲል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ ።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመላው የክልሉ ሕዝብ ለሻደይ፣ አሸንድየ፣ ሶለል እና ቡሔ በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ ከነሐሴ ወር ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር በመጣው ትውፊት መሰረት የምስጋና በዓላትን በአደባባይ ወጥቶ ማክበሩ ለዘመናት የቆየ ባህላዊ እሴቱ መሆኑን አመላክቷል፡፡
“ባህላዊ እሴቶቻችንን ከአባቶቻችን እንደተቀበልን ሳይበረዙ ለትውልድ የምናሻግራቸው የማንነታችንና የአንድነታችን መገለጫዎች ናቸው” ብሏል የክልሉ መንግሥት በመልዕክቱ።
“እሴቶቻችን የሕዝባችንን ጥንታዊ ትውፊት ጠባቂነት ከማስመስከር በተጨማሪ የባህላዊ እሴታችንን ተዋኅዶ እና አንድነት ጎልቶ የሚታይባቸው ሀብቶች ናቸው” ብሏል፡፡
ሻደይ፣ አሸንድየ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ፣ እንቁጣጣሽ/የዘመን መለወጫ እና ቡሔ ሕዝቡ የሚደምቅባቸው በዓላት÷ የባህላዊ እሴቶቻችን የማይነጠል ውኅደትና አንድነት ማሳያ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዓላቱን ስናከብር÷ “እንደ እንግዳ ደራሽ፤ እንደ ውኃ ፈሳሽ” ድንገቴ ያገኘናቸው ሳይሆኑ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ያስረከቡን ባህላዊ እሴቶቻችን መሆናቸውን ልብ ልንልና መጪውን ትውልድ በአንድነት ጸንቶ እንዲቆም ለማድረግ የምንጠቀምባቸው ሊሆኑ ይገባል ሲል የክልሉ መንግሥት አጽንዖት ሰጥቷል፡፡
እነዚህን እሴቶች ለማጥፋት “እኛ እናውቅላችኋለን” የሚሉ የሕዝባችን አንድነት ጠላቶችን በጋራ በመመከት ለሕዝባችን እፎይታን በማምጣት ትኩረቱን ሁሉ ሁለንተናዊ ብልጽግና ላይ እንዲያደርግ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት መረባረብ መሆን ይገባልም ብሏል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.