Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ÷ በግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን በወጣው አዋጅ እና የዕጽዋት ዘር ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል እንዲጸድቁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ከአምራቾች ጋር በሚደረግ ውል የግብርና ምርቶችን በስፋት ማምረት እንዲቻል፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ÷ የእውቀት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን መሰረት በማድረግ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።

በተጨማሪም የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት የአምራች እና የአስመራች ግንኙነት በተሟላ የሕግ ማዕቀፍ የሚመራበት ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችልም ነው የተመለከተው።

በዚህም መሰረት የአምራቾችን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያስችል ህግ ማውጣት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበው መሰረት ነው ውይይት የተደረገው፡፡

እንዲሁም በሥራ ላይ ያለው የዕጽዋት ዘር አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 782/2005) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ከምትገኘው ዘርፈ ብዙ የግብርና እመርታዎች ጋር ሲታይ ክፍተቶች ያሉት መሆኑ ተገልጿል፡፡

አሁን የግብርናው ዘርፍ ከደረሰበት ደረጃ አኳያ የዕፅዋት ዘር አቅርቦትን በጥራት፣ በዓይነትና በመጠን በዘላቂነት ማምረት እንዲቻል÷ የአገሪቱ የዕፅዋት ዘር ኢንዱስትሪን ለማዘመን፣ ቴክኖሎጂና ኢንቨስትመንት በመሳብ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑ ነው የተጠቆመው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ላሉ አግሮ ኢንደስትሪዎች የግብዓት አቅርቦት ለማሳደግ፣ መጠባበቂያ የእጽዋት ዘር አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት እና ተያያዥ አስቻይ ሁኔታዎችን ለማሟላት ይቻል ዘንድም የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.