Fana: At a Speed of Life!

በኢኮኖሚ፣ ህዳሴ ግድብና አረንጓዴ አሻራ የተገኙት ስኬቶች ኢትዮጵያ በስኬታማ የከፍታ ጉዞዋ መቀጠሏን ያሳዩ ናቸው – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢኮኖሚ፣ ህዳሴ ግድብ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ በሰላምና ፀጥታ ዘርፎች የተገኙት ስኬቶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የመጨረስ አቅም እንዳላት፤ በስኬታማ የከፍታ ጉዞዋ መቀጠሏን ያሳየችባቸው መሆናቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢኮኖሚ አፈፃፀም እና ከሰሞኑ ስለተጠናቀቁት የህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እና የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻዎች አብራርተዋል።

በማብራሪያቸውም ሀገሪቱ በታሪኳ አይታው በማታውቀው ሁኔታ ከወጪ ንግድ 10 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቷን ጠቁመዋል።

በዚህ የገቢ ግኝት ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ግንባር ቀደም ድርሻ እንዳለው ተመልክቷል።

በበጀት ዓመቱ ውስጥ መንግስት 336 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብም ስኬታማ አመት አሳልፏል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅትም የግብርናው ዘርፍን ምርታማነት የማሳደጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን በመጠቆም፥ ለአብነትም የትግራይ ክልልን ጨምሮ ሁሉም አካባቢዎች ግብዓት እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።

አሁን ላይ አብዛኛው እርሻ በዘር መሸፈኑ ነው የተነሳው።

የስንዴን ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ እና አብዛኛው እርሻም በኩታ ገጠም እየለማ ስለመሆኑ በሚኒስትሩ መግለጫ ተጠቅሷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ እና ሁለተኛው ተርባይን ወደ ሀይል ማመንጨት መሸጋገር ሌላው ስኬት ነው።

ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ የተቋጨው አረንጓዴ አሻራ ስራን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማፅደቅ ቀሪው ስራ መሆኑንም ነው በመግለጫቸው ያመለከቱት።

እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ እያለፈች የማትሰበር፣ ዜጎቿም ችግር የማይገታቸው እና ታሪካዊ አሻራ የሚያኖሩ መሆናቸውን  እንደሚያሳዩ ዶክተር ለገሰ ተናግረዋል።

 

በስኬቶች እና በድሎች በመታጀብ አዲሱን ዓመት እንቀበላለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.