ሚድሮክ በ750 ሚሊየን ብር የገነባው የ“ቺፕስ” ፋብሪካ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ750 ሚሊየን ብር ወጪ በሐዋሳ ከተማ የገነባው የ“ቺፕስ” ፋብሪካ ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ ስፈፃሚ አቶ ጀማል አሕመድ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት÷ ፋብሪካው በጀመሪያ ዙር ሥራው ለ242 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ፋብሪካው በቀን 36 ቶን ድንች የመፍጨት አቅም እንዳለው ጠቁመው÷ ይህም በሐዋሳ ከተማና አካባቢዋ ለሚገኙ ድንች አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው ብለዋል፡፡
የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ እንደገለጹት÷ ሚድሮክ በሐዋሳ ከተማ እያደረገ ያለው ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ባለፈ የከተማችንን ቱሪዝም ከፍ እንዲል አድርጓል።
ለኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ያላለሙ ግለሰቦችና ተቋማት ወደ ልማት መግባት እንዳለባቸው አሳስበው÷ ወደ ከተማችን ለሚመጣ ማንኛውም አልሚ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የ “ቺፕስ” ፋብሪከው ሠራተኞች በበኩላቸው÷ የችብስ ፋብሪካው በአካባቢው ያልተለመደ መሆኑን ጠቁመው አዲስ የሥራ ባህልን እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡
በጥላሁን ይልማ