Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ መሠል የቤት መደርመስ አደጋ እንዳይከሰት የቤቶች ጥገናና እድሳቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን መሠል የቤት መደርመስ አደጋ እንዳይከሰት የጀመረውን የቤቶች ጥገናና እድሳት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

በትናንትናው ዕለት በመዲናዋ መርካቶ መሀል አዳራሽ አካባቢ ለሱቅ እና ለመጋዘን አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘውና የኮርፖሬሽኑ ንብረት የሆነው የንግድ ቤት የፈትለፊት የግንባታ አካል ፈርሶ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ባስከተለው ጉዳት ኮርፖሬሽኑ የተሰማውን ሐዘን ገልጿል፡፡

በዚኅም ኮርፖሬሽኑ አደጋው ከደረሰ ሰዓት አንስቶ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያቀፈ አስቸኳይ ግብረ ሀይል አቋቁሞ ወደ ሥራ የገባ መሆኑ የገለፀ ሲሆን÷ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚህም ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማና የወረዳ 8 አመራሮች እንዲሁም ከተከራይ ደንበኞች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ÷በቀጣይም ወቅቱ የክረምት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ጥገናና እድሳት የሚያስፈልጋቸውን ቤቶች የልየታ ሥራ ማከናወኑን ገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳደራቸው ቤቶች በስፋት የጀመረውን የእድሳት እና የጥገና ሥራዎችን፣ ከተከራይ ደንበኞቹ ጋር በጋራ በመሆን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡

እንዲሁም የመናድ አደጋ የገጠመውን የንግድ ቤት አጠቃላይና አስፈላጊውን የጥገናና አድሳት ሥራ በማድረግም ለአገልግሎት እንደሚያበቃ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.