Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል በጎርፍ አደጋ ከ4 ሺህ በላይ ወገኖች ተፈናቅለዋል- የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በአራት ወረዳዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ4 ሺህ በላይ ወገኖች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታወቀ።

የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን÷ በክልሉ ደጋማው አካባቢ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በላሬ፣ በመኮይ በዋንቱዋና በኢታንግ ልዩ ወረዳ ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ተናግረዋል።

የጎርፍ አደጋው ከደረሰባቸው ወረዳዎች ከ4 ሺህ በላይ ወገኖች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ጠቅሰው÷ ተፈናቃዮቹን ለጊዜው ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች እንዲጠለሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በአደጋው በኢታንግ ልዩ ወረዳ 2 ሺህ 40 ወገኖች፣ በላሬ ወረዳ 1 ሺህ፣ በዋንቱዋ ወረዳ 619 እንዲሁም በመኮይ 480 ዜጎች ተፈናቅለዋል ነው ያሉት፡፡

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተፈናቃዮቹ የጎርፍ አደጋው ሲከሰት ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ መጠለላቸውን ጠቅሰው፥ መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.