Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ታንዛንያ አቀና

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት ወደ ታንዛንያ አቅንቷል፡፡

ዋልያዎቹ በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን)  ጨዋታ ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር  የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ለማድረግ ነው  ወደ ታንዛንያ ያመሩት፡፡

ሰባተኛው የቻን የእግር ኳስ ውድድር በጥር እና የካቲት ወር 2015 ዓ.ም በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

ዋልያዎቹ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ነሐሴ 20 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከሩዋንዳ አቻው ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ከነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለጨዋታው ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም በቻን የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን በድምር ውጤት 5 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ የዋልያዎቹ ተፋላሚ  የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን 24 ተጫዋቾችን በመያዝ ዛሬ ወደ ታንዛንያ እንደሚያመራ ተጠቁሟል፡፡

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከነገ በስቲያ በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የተሳታፊዎች ቁጥር በመጨመር ከዚህ ቀደም በሻምፒዮናው የሚሳተፉ 16 ሀገራትን በአልጄሪያው ውድድር ወደ 18 ከፍ አድርጓል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.