Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር አብርሃም በላይ ለትግራይ ሕዝብና ወጣት የሰላም ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው በመነጋገር፣ በመወያየትና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብሃም በላይ ለትግራይ ወጣቶች የሰላም ጥሪ አቀረቡ።
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ለትግራይ ሕዝብና ወጣት ቅንጣት ታክል ደንታ የሌለው የጥፋት ኃይል የሆነው የህወሓት ቡድን ፥ ካለፈው እልቂት፣ አሳር፣ መከራና ውድመት ሳይማር አሁንም ሮጠው ያልጠገቡ ሕጻናትና ወጣቶችን ወደ አዲስ ዙር ጦርነት እየማገዳቸው ይገኛል ብለዋል።
የፌደራል መንግስት ለሰላም ያሳየውን ዝግጁነትና ያቀረበውን ጥሪ የጥፋት ቡድኑ ወደጎን በመተው÷ የትግራይ ሕዝብ ተስፋ ያደረገበትንና በጉጉት ሲጠብቀው የቆየውን የሰላም አማራጭ በመተው ዛሬ ጦርነት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
አክለውም “የተከበርክ የትግራይ ሕዝብና ወጣት÷ የጥፋት ኃይሉ ህወሓት የጀመረውን የውድመትና የጥፋት መንገድ ኮንነህ፣ ጦርነት አቁሞ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለስ ጫና መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል“ ብለዋል፡፡
ይህ በጎ ተግባር በየትኛውም የዓለም ጫፍ የሚገኝ እያንዳንዱ ትግራዋይና የትግራይ ሕዝብ ወዳጅ ሥራ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ የጦርነትን ትሩፋትና ጠባሳ እንዲሁም የሰላምን አስፈላጊነት እና ጥቅም ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕዝብ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ ሕጻናትና ወጣቶችን ወደ እሳት እየማገዱ የሚገኝ ጥቅም አለመኖሩ ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል፡፡
አሁንም “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ አበው÷ ሳይረፍድ የሰላም ዘብ ሆኖ መቆም ለነገ መባል የሌለበት ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የትግራይ ወጣት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.