Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ለዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለፃ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጡ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶችን በስፋት አብራርተዋል።

በገለጻቸውም ፥ በመንግሥት ለሰብአዊ ድጋፍ ሲባል የተደረገውን የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔና ያልተገደብ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት የተደረጉ ጥረቶችን ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል።

መንግስት የሦስተኛ ወገን ስምምነት በተመድ ጽ/ቤት በመፈረም እንዲሁም ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የአደጋ ጊዜ እና የማገገሚያ ፕሮጀክት በትግራይ ክልል ተግባራዊ እንዲደረግ መስማማቱን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የህወሓት ቡድን መንግስት የወሰዳቸውን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን በመተው ጦርነት መክፈቱንና የሚደርሰውን እርዳታም ለጦርነት እያዋለው መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ቡድን በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ የተጀመረውን የሰላም ጥረት በመግፋት ወደ ጦርነት መግባቱን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ይህን ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝ እንዲሁም ቡድኑ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

መንግሥት በንጹኃን ዜጎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እና ጥፋት እንዳይደርስ ቅድሚያ በመስጠት አሁንም ለሰላም አራጭ ዝግጁ መሆኑንም አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ፥የአገሪቱን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.