Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘሁ አለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በተጠናቀቀው  በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በሰጡት መግለጫ ፥ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተሰማሩ ባለሃብቶች ወደ ውጭ ከላኳቸው ምርቶች 196 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

አፈጻጸሙም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አንስተዋል።

ለሀገር ውስጥ ገበያ ስትራቴጂካዊ ምርቶችን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ጫናን ለመቀነስ መሰራቱን የገለፁት ስራ አስፈፃሚው ፥ በዚህም 161 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ከሀገር ውስጥ ምርት አቅራቢ ድርጅቶችና አርሶ አደሮች ጋር በተፈጠረ ትስስርም ከ69 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ግብዓት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ማቅረብ መቻሉንም አብራርተዋል፡

ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ከመስሪያና መሸጫ ቦታ ኪራይ፣ ከቢሮ አቅርቦት እና ሌሎች አገልግሎቶች 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ከአጎአ ተጠቃሚነት መሰረዟ፣ በሀገር ውስጥ በነበረው ጦርነት አምስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በደረሰባቸው ውድመት ማምረት ማቆማቸው ለኮርፖሬሽኑ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመሟላት እንዲሁም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትም በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ፈተናዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ57 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንም ዋና ስራ አሰፈፃሚው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.