Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ውጤት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የ2014 የትምህርት ዘመን ክልላዊ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ተደረገ።

የደቡብ ክልል እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 257 ሺህ 45 ተማሪዎች መካከል ከ73 በመቶ በላይ ተማሪዎች ማለፋቸውን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቋል።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ የሁለቱንም ክልሎች የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በ2014 የትምህርት ዘመን በሁለቱም ክልሎች 257 ሺህ 45 ተማሪዎች ፈተና ወስደው 187 ሺህ 567 ተማሪዎች ማለፋቸውን ገልጸዋል።

የክልላዊ ፈተናው ውጤት በሁለቱም ክልሎች የጋራ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፥ የትምህርት ጥራት ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ታሳቢ ያደረገ ውጤት መሆኑንም ጠቁመዋል።

አክለውም በትምህርት ዘመኑ በሁለቱም ክልሎች የተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ፣ የቀደሙ ውጤቶችን የተመለከተና የሌሎች ክልሎችን ልምድም በመውሰድ የተወሰነ ውጤት ነው ብለዋል።

በዚህም በሁለቱም ክልሎች ውሳኔ መሰረት የማለፊያ ነጥብ መቀመጡን የገለጹት ሀላፊው ለወንዶች 41፣ ለሴቶች 40 እና ለአይነ ስውራን 39 እንዲሆን መወሰኑንም ነው የገለጹት።

በተለየ መልኩ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በአሉታዊ ጫና ውስጥ ሆነው የተማሩና ለፈተና የተቀመጡ የደራሼ ልዩ ወረዳ ተማሪዎችን ውጤት በተለየ መልኩ ለማየት መሞከሩን ገልጸው ፥ ለወንዶች 39፣ ለሴቶች 38 እና ለአይነ ስውራን 37 መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የሁለቱ ክልሎች ተማሪዎች ውጤታቸውን ከነገ ጀምሮ መውሰድ ይችላሉ ነው ያሉት።

የደራሼ ልዩ ወረዳ ተማሪዎች ግን ውጤታቸው በእጅ የሚሰራ በመሆኑ የአንድ ሳምንት ጊዜ እንዲጠብቁም ጠይቀዋል።

በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ፈተና ሀገር አቀፍ የሚደረግ በመሆኑ ሁሉም የትምህርት ማህበረሰብ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት ዝግጅት ሊያደርግ ይገባል ማለታቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.