ለ10 ሚሊየን ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 አመታት ለ10 ሚሊየን ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ፕሮጀክቱ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን እና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን አማካኝነት ነው ይፋ የተደረገው።
የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነሩ ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ወጣቶችን የስራ ባለቤት ለማድረግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
አያይዘውም መንግስት ወጣት እና ሴቶችን የስራ ባለቤት ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ስራ አስፈጻሚ ሪታ ሮይ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ያለውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 300 ሚሊየን ዶላር በጀት ተይዞለታል።
የአሁኑ ፕሮጀክት ፋውንዴሽኑ በአፍሪካ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ 1/3 የሚሸፍን ነው ተብሏል።
በአዳነች አበበ