Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ወታደራዊ ጥቃት አባብሶ ቀጥሏል – መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ሕወሓት የሰላም አማራጮችን ሁሉ ረግጦ የከፈተውን ወታደራዊ ጥቃት አባብሶ መቀጠሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ አሸባሪው ሕወሓት የተዘረጋለትን የሰላም አማራጭ ረግጦ ለሦስተኛ ጊዜ በሀገራችን ላይ የከፈተውን ወታደራዊ ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሎበታል ብሏል፡፡

አሸባሪው ለሰላም የተዘረጋውን መንገድ ትቶ፣ በሙሉ አቅሙ ለጦርነት ሲዘጋጅ መቆየቱ ይታወቃልም ነው ያለው።

አሁንም በተለያዩ ግንባሮች የከፈተውን ጥቃት አድማሱን በማስፋፋት ለፍቶ አዳሪ ንጹሐን ዜጎችን ዒላማ እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

ጊዜ ያለፈበትን የሰው ማዕበል የጦርነት ስልት በመከተል በሺዎች የሚቆጠሩ አዳጊዎችንና ወጣቶችን በገፍ እየማገደ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የከፈተውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ዛሬም አጠናክሮ ቀጥሏልም ነው ያለው በመግለጫው፡፡

ሕወሓት ግድያ፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ማውደም፣ መሠረተ ልማት የማፈራረስና መሰል የጭካኔ ተግባራትን ለመፈጸም እንደ ከዚሀ ቀደሙ ሁሉ ኃይል አሰባስቦ ወደ አማራና አፋር ክልል አዋሳኞች እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አንስቷል።

መገግሥት የዘረጋው የሰላም አማራጭ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይሀ አሸባሪ ቡድን የከፈተውን መጠነ ሰፊ ጥቃት በተሟላ ብቃት በመመከት ላይ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.