Fana: At a Speed of Life!

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የደንበኞች የኔትወርክ አገልግሎት ሙከራ በድሬዳዋ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ተከታታይ የደንበኞች የኔትወርክ አገልግሎት ሙከራ በድሬዳዋ ከተማ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የደንበኞች የሙከራ ምዕራፍ፥ ኩባንያው በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት ከሚዘጋጅበት ጊዜ አስቀድሞ በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች የኔትወርክ እና የአገልግሎት ጥራቱን በተጠናከረ ሁኔታ የሚፈትሽበት ሂደት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራ በ2G፣ 3G እና 4G ኔትወርኮች የሚካሔድ ሲሆን÷ ደንበኞች በ07 በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መስመር የስልክ ቁጥሮቻቸውን መርጠው ሲም ካርድ መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል፡

ደንበኞች የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሲም ካርዶች የድርጅቱ መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች ማግኘት እንደሚችሉ እና ኔትወርኩን ለአንድ ወር ያህል እንዲሞክሩት የሚረዳ የደንበኝነት ማስጀመሪያ የዳታ፣ የድምጽ እና የጽሑፍ መልዕክቶች ጥቅል ያገኛሉም ተብሏል፡፡

የደንበኝነት ማስጀመሪያ ጥቅሉ በሚያልቅበት ጊዜ ደንበኞች የአየር ሰዓት ከሽያጭ ማዕከላት ወይም መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች በመግዛት መሙላት እና አገልግሎቱን በቀጣይነት መጠቀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አገልግሎት በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሙከራ ኔትወርክ ደንበኞች፥ ዳታ መጠቀም፣ ጥሪዎች እና የጽሑፍ መልዕክቶችን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጋር መለዋወጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ እንደሚችሉ መገለጹን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.