መከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተወካዮች ማብራሪያ እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የውጭ ግንኙነት ክፍል በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በኢትዮጵያ ላሉ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተወካዮችና የሰላምና ፀጥታ ኃላፊዎች እንዲሁም ለሀገራት ወታደራዊ አመራሮች ማብራሪያ እየሰጠ ነው።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ጀነራል ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ ÷የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ ማናቸውም አይነት የጥፋት ሙከራዎችን በአስተማማኝ መልኩ መቀልበስ እና መመከት የሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የህወሓት የሽብር ቡድን የሰላም አማራጮችን በመግፋት የኢትዮጵያ ጦር ላይ ዳግም ጥቃት መክፈቱን ይህም የሽብር ቡድኑ ለሰላም ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳይ እንደሆነ ሜጀር ጀነራል ተሾመ ለወታደራዊ አመራሮቹ አብራርተዋል።
ህወሓት የጀመረው ጦርነት በቴክኖሎጂ መረጋገጥ የሚችል እንደሆነ የሽብር ቡድኑ በወትወት ራማ ቢሶበር እና ዞብል እንዲሁም በአፋር ድንበር ጦርነት መክፈቱን ገልፀዋል።
መከላከያ ሰራዊት የሀገሩን ዳር ድንበር የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት ያነሱት ሜጀር ጀነራል ተሾመ ÷ መከላከያ እንደ አንድ ቁልፍ የብሄራዊ ማስፈፀምያ አቅም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በተለይም የህልውና ጥቅም የማስከበር ተቋማዊ ግዴታ አለበት ብለዋል።
ስለሆነም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነት ለሰላም የተከፈለውንም ዋጋ መረዳት እና ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም እንደሚገባው ማብራራታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡።
በሽብር ቡድኑ በሚፈበረኩ የተዛቡ መረጃዎችም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊሳሳት እንደማይገባው ጥቃቱ እንዴት እንደተጀመረ በቀላሉ መለየት እንደሚቻል አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሰራዊትም በሽብር ቡድኑ የተቃጣበትን ጥቃት በአግባቡ እየመከተ እንደሆነና ለዚህ ደግሞ የማንም ፍቃድ እንደማያስፈልገው ነው ያስገነዘቡት ።