Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ከ67 በላይ የበርበሬ መሸጫ ሱቆች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ቢሮው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ሱቆችን መዝጋቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ሳኒታይዘር፣ አልኮል፣ የፊት ጭምብልና ሌሎች ግብዓቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ፋርማሲዎች ላይ እርምጃ ተወስዷልም ነው ያሉት።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ ማስኮችን ጨምሮ የተለየዩ ንብረቶች መወረሳቸውንም ገልጸዋል።

አያይዘውም ቢሮው መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን ባቋቋመው ግብረ ሃይል መለየቱን ጠቅሰው፥ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ምክትል ሃላፊው በሌሎች ሃገራት አምራችና አከፋፋዮች መሰል አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ፥ ትርፍ እየቀነሱ በመሸጥ ሃገራዊና ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውሰዋል።

በተያያዘ ዜና በመዲናዋ የፊት ጭምብል (ማስክ) በ500 ብር እንሸጣለን በማለት ሲያስተዋውቁ የተገኙ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ግለሰቦቹ በማህበራዊ ትስስር ገጽ /ፌስ ቡክ/ በተጋነነ ዋጋ ጭምብል እንሸጣለን በሚል በለጠፉት ማስታወቂያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተገለጸው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተደረገ የማጣራት ሂደት ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠ መድሃኒት በግለሰቦቹ መጋዘን ውስጥ ተገኝቷልም ነው የተባለው።

በፋሲካው ታደሰ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.