Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ ወቅታዊ የደህንነት ሥጋቶችን የሚመክቱና ቀጣይ አደጋዎችን የሚያስቀሩ ክለሳዎች አካሄድኩ አለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በ2014 የበጀት ዓመት በሀገር ላይ ያጋጠሙን ወቅታዊ የደህንነት ሥጋቶችን በሚገባ የመከቱና ቀጣይ አደጋዎችን ማስቀረት የሚችሉ የተልዕኮ ክለሳዎችን መሠረት ያደረጉ ስምሪቶች ማካሄዱን አስታወቀ።

ተቋሙ በህግ ማስከበሩ ሂደት፣በህልውና ዘመቻውና በ2014 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ከተቋሙ ጋር በቅንጀትና በመተጋገዝ ለሰሩ ለፌደራልና ለክልል የፀጥታ አካላትና ለሌሎች ባለድርሻዎች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የክልል ርዕሳን መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የመረጃ ተቋማት አመራሮች፣የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት ፥ የምስጋናና እውቅና መድረኩ ዓላማ ጠንካራ ተሞክሮዎችን በማስፋት ለቀጣይ ሃገራዊ ተልዕኮዎች ተነሳሽነት ለማጎልበት እንዲሁም ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ አካላትና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የተጀመረውን መተጋገዝ፣ አንድነትና ግንኙነት ማጠናከር ነው፡፡

በ2014 ዓ.ም የሥራ ዘመን የተቋሙ ተልዕኮዎች ላይ ክለሳ በማድረግ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣በመረጃ ስምሪት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በአጋርነትና ትብብር ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧልም ብለዋል አቶ ተመስገን።

ተቋሙ ወቅታዊና ቀጣይ የደህንነት ሥጋቶችን መሠረት ያደረጉ የተልዕኮ ክለሳዎች በፍጥነት በማካሄዱና ወሳኝ የሆኑ የአቅም ግንባታ መስኮችን በመለየት ወደ ተግባር መሸጋገሩ ለውጤቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አቶ ተመስገን አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው ፥ የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት የመረጃ ስምሪትና ተሳትፎ አሁን እየተካሄደ ያለውን ፀረ አልሸባብ ዘመቻ ውጤታማ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በ2014 የሥራ ዘመን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአዲስ ምዕራፍ ላይ የተራመደበት፣ ለአዳዲስ ተልዕኮዎች ራሱን ያበቃበት፣ መጪውን ዘመን የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ራሱን ያዘጋጀበት፣ ከፊቱ ያሉትን ዕድሎችና ሥጋቶች በሚመጥን መልኩ ለነገ ራሱን ዝግጁ ያደረገበት እንደሆነ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.