Fana: At a Speed of Life!

ጭንቀት፣ ምልክቶቹ እና መፍትሄዎቹ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለማሳካት የምንፈልጋቸው ነገሮች ከዓቅማችን በላይ ሲያሳስቡን እና ስናውጠነጥን የሚፈጠር ከገደብ ያለፈ ስሜት፥ ጭንቀት ነው ተብሎ ሊበየን ይችላል።

ጭንቀት ከፍላጎቶቻችን ወይም ከሁኔታዎች ጋር ራሳችንን ማጣጣም ሲከብደን የሚፈጠር ስሜት ነውም ሊባል ይችላል፡፡

አንድ ሰው ጭንቀቱን መቆጣጠር ሲከብደው ሥር ወደሰደደ ሕመም ሊያመራው እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ውጥረት የበዛበት የሥራ ሁኔታ እና ከባቢ፣ ሰዎች ከሰዎች ጋር የሚኖራቸው ያልተመቸ ግንኙነት እና መስተጋብር ፣ ከኢኮኖሚ እና ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አጣብቂኝ ሁኔታዎች እና የመሳሰሉት ጭንቀት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

ጭንቀት የፀጉር መነቃቀል እና መመለጥ ፣ የእንቅልፍ እጦት፣ ራስ ምታት ፣ መነጫነጭ ፣ መደበት እና የተለያዩ የባኅሪ ለውጦች ሊያስከትል ይችላል፡፡

ጭንቀት ለደም ግፊት መጨመር፣ ለልብ ሕመም ፣ በጡንቻዎች ላይ ለሚፈጠር የሕመም ስሜት ፣ ለወገብ እና ጀርባ ሕመም ፣ ለጨጓራ ሕመም እንዲሁም ለአንጀት ቁስለትም መንሥዔ ሊሆን እንደሚችልም የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በከንፈር ላይ የሚወጡ አንዳንድ ቁስለቶችም ከጭንቀት ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ፡፡

የአስም ሕመምተኞች ሕመማቸው እንዲነሳባቸው ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች አንዱ ጭንቀት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ከጭንቀት ለመወጣት

አካላዊ እንቅስቃሴ መሥራት ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ እና በሽታ የመከላከል ዐቅም መገንባት፣ የሚወሰዱ የአልኮል መጠጦች እና አነቃቂዎችን እንዲሁም የተለያዩ መድሐኒቶችን መቀነስ ከጭንቀት ለመውጣት አስቻይ መንገዶች ናቸው ተብሏል፡፡

የተለያዩ የኤሮቢክስ ስፖርቶችን ማዘውተር፣ መዝናናትና መዋኘትም ጭንቀትን ለማስወገድ ሚናቸው ቀላል አለመሆኑን ሜዲካል ኒውስ ቱደይ በመረጃው ጠቁሟል፡፡

የአንድ ሰው ጭንቀት ከላይ በተጠቀሱት የመፍትሄ ሃሳቦች የማይመለስ ከሆነና ሥር ከሰደደ ሐኪም ዘንድ በመቅረብ እና በማማከር ለችግሩ መፍትሄ የሚያገኝበት መንገድ እንዳለም ተጠቁሟል፡፡

ሐኪም በማማከር የሚወሰዱ የተለያዩ መድሐኒቶችም አሉ ፡፡

የዘርፉ የሕክምና ባለሙያዎች መድሐኒት የሚያዙት ግን፥ ከላይ የተገለጹት መፍትሄዎች ተግባራዊ ተደርገው ውጤት ካላስገኙና የመጨረሻ አማራጭ ነው ብለው ካመኑበት ብቻ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.