Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ 28 ቋንቋዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ 28 ቋንቋዎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገለፀ።
 
በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በቋንቋ ፖሊሲ ላይ የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን፥ በመድረኩ ላይ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት ሁሉም ቋንቋዎች እኩል መብት ተሰጥቷቸው የለሙ መሆናቸው ተነስቷል።
 
በዚህም አሁን ላይ ከ50 በላይ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ለማስተማሪያነት እያገለገሉ እንደሚገኙም ነው የተገለፀው።
 
ሆኖም በሀገሪቱ ለቋንቋዎች እድገት ስርዓት ባለመበጀቱ በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዳልመተዘገበ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
 
በኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋዎች ቢኖሩም ብዝሃ ልሳን ያለው ማህበረሰብ መፍጠር አልተቻለምም ተብሏል።
 
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) መረጃ አሁን ላይ በኢትዮጵያ 28 ቋንቋዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
 
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም በቅርቡ የቋንቋ ፖሊሲ የፀደቀ ሲሆን፥ በመድረኩ ላይ በፖሊሲው ይዘትና አተገባበር ላይ ውይይት ተደርጓል።
 
በቋንቋ ፖሊሲ ይዘትና አተገባበሩ ላይም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አቶ አውላቸው ሹምነካ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር እዮብ ይገዙ እና ዶክተር ታዬ አበራ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
 
በዚህም የቋንቋ ፖሊሲው በውስጡ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፥ የስራ ቋንቋ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ቋንቋ አጠቃቀም፣ ቋንቋ እና ትምህርት፣ የአደባባይ ቋንቋ አጠቃቀም እንዲሁም ትርጉምና አስተርጓሚነት በፖሊሲው ከተዘረዘሩት ዋነኞቹ ናቸው።
 
በፖሊሲው አሁን ያለውን አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ አምስት ቋንቋዎች በስራ ቋንቋነት እንዲያገለግሉ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፥ አፈፃፀሙም በህገ መንግስት ማሻሻያ የሚታይ ይሆናል ነው የተባለው።
 
የአደባባይ ቋንቋን በተመለከተም እስካሁን በኢትዮጵያ የማስፈፀሚያ ስርዓት ባለመኖሩ በመሪዎች ደረጃ ጭምር የቋንቋ አጠቃቀም ወጥ እንዳልነበረ ተነስቷል።
 
ፖሊሲው ይህንን እና ሌሎች ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተገለፀው።
 
በምሁራኑ እንደተገለፀው ፖሊሲውን ተቋማዊ ለማድረግ ብሄራዊ የቋንቋ ጉዳዮች ምክር ቤት፣ የቋንቋዎች ጥናት ማዕከሎች እና የትርጉም ተቋም መመስረት ያስፈልጋል።
 
በአላዛር ታደለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.