Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ የሜጢ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤል ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ የሜጢ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት ግንባታው የተጀመረው የሜጢ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አሁን ላይ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ÷ ክልሉ ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ ሃብት ያለበት ቢሆንም የክልሉ ህዝብ የሃብቱን ያህል ተጠቃሚ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሜጢ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር በመኖሩ ምክንያት የተወሰነ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የመጀመሪያ ምዕራፍ ርክክብ መደረጉንም አመላክተዋል።

በቀጣይም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥና የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲቀረፍ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት፡፡

የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሪያል ጂንግ በበኩላቸው÷ የሜጢ ከተማን ህዝብ ዘላቂና አስተማማኝ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ መጠናቀቁን የገለጹት ሃላፊው÷ ቀሪውን ለማጠናቀቅ 48 ሚሊየን ብር መመደቡንና ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ25 ሺህ በላይ የሜጢ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.