Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን የሚያተራምሱ አካላትን በጋራ መከላከል እንደሚያስፈልግ የድሬዳዋ አስተዳደር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት ለመጠበቅ ኢትዮጵያን የሚያተራምሱ አካላትን በጋራ መከላከል እንደሚያስፈልግ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡

በአሸባሪው ህወሓት የተከፈተውን ጦርነት አስመልክቶ “ለሀገር ክብር በትግል እናብር ” በሚል መሪ ሀሳብ ለሐይማኖት አባቶች፣ ለአባ ገዳዋች፣ ለኡጋዞች፣ ለሀገር ሽማግሌዋች በድሬዳዋ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጆሀር÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የተዘረጋለትን የሰላም እጅ ወደ ጎን በመተው ጥቃት መፈፀሙን ጠቅሰው÷ ወረራውን ለመመከት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዲችል መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ቡድኑ የጀመረውን ጥቃት በመመከት መንግስት የያዘውን አቋምና የሰላም አማራጭ በመጠቀም የህዝቡን ሰላም ለመጠበቅ መስራት አለብንም ነው ያሉት፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል እንዲሁም የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት ለመጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዋችን ማስቀጠል እንዳለባቸውና በጦርነቱ የሚደርሰውን የኢኮኖሚ ጫና መቋቋም እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ የመከላከያ ሰራዊት ለሚያደርገው ተጋድሎ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፖለቲካው ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚ ላይ ጫና ለመፍጠር በሀገሪቱ ላይ ጥቃት መፈፀሙን በሚመለከትና እንደ ሀገር የመንግስትን አቋም የያዘ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.