አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የተለያዩ ሀላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
አምባሳደር ሂሩት በአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂንሃ፣ የአውሮፓ የዜጎችና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቢሮ የሰሐራ በታች፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካና ፓስፊክ ዳይሬክተር አንድሪያ ኩላይማ እና የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ተጠባባቂ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሃንስ ስታውስቡል ጋር ነው የተወያዩት።
በውይይታቸውም፥ አምባሳደሯ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን ለሌላ ዙር ጦርነት የዳረጋትን የአሸባሪውን ህወሓት ጠብ አጫሪ ድርጊት በማያሻማ መልኩ እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።
በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የሰላም ውይይት ሂደትም መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት አስረድተዋል።
የውይይት መድረኩ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በግልጽ ለማስረዳት ፋዳው የጎላ መሆኑን በቤልጂየም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡