Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ጤና ድርጅት የዶክተር ቴድሮስን ከድርጀቱ ስነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት በፍጥነት እንዲያስቆም ኢትዮጵያ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት ስራ አስፈፃሚ ቦርድ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከተቋሙ ሰራተኞች ስነ ምግባር በተፃረረ መንገድ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሀሰት መረጃ የማሰራጨት ድርጊትን እንዲያስቆም በጄኔቫ የኢትዮጵያን ቋሚ መልዕክተኛ ጽኅፈት ቤት ጠየቀ።

ቋሚ መልዕክተኛ ጽኅፈት ቤቱ፥ ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያሰራጫቸው የሐሰት መረጃዎች እና ፕሮፖጋንዳዎች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ጽኅፈት ቤቱ በጋዜጣዊ መግለጫው፥ በፈረንጆቹ ኅዳር 3 ቀን 2020 አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ጦር ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሷል፡፡

ጥቃቱ ከተፈፀመ ጀምሮም ከህወሓት ጉምቱ አመራሮች መካከል ሥሙ የሚጠቀሰው ዶክተር ቴድሮስ፥ በተናበበ እና በህወሓት የዕዝ እና የቁጥጥር ሠንሠለት ሥር ሆኖ ትዕዛዝ በመፈፀም የሽብር ቡድኑን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሲያሠራጭ መቆየቱን አመላክቷል፡፡

መግለጫው አመቺ ናቸው ባሏቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ዶክተር ቴድሮስ አድኀኖም ህወሓት የሚፈፅማቸውን ሕገ-ወጥ ተግባራት ሲደግፍ ተስተውሏልም ነው ያለው ፡፡

ዶክተር ቴድሮስ፥ ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ተቋማትን፣ የህዝብ አገልግሎት ተቋማትን እና መሠረተ-ልማቶች ሲያወድም በፍፁም ሲኮንን እና ሲያጋልጥም ታይቶም ተሰምቶም እንደማይታወቅም አስታውሷል፡፡

ዶክተር ቴድሮስ አብዝቶ የሚደግፈው ይህ ቡድን አሁንም በአጎራባች ክልሎች ላይ የፀብ-ጫሪ ተግባሩን መቀጠሉን አመላክቷል፡፡

ባለፈው ወረራ የፈጸማቸውን የህዝብ ተቋማት የማውደም ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን የመፈጸም እና የመጨፍጨፍ ተግባራት አሁንም በክልሎቹ መቀጠሉንም አውስቷል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ የሰብዓዊ እና ቤተሰብ ጉዳይ በማስመሰል በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ ያለውን ስልጣን የኢትዮጵያን መንግስት ስም ለማጥፋት እየተጠቀመ መሆኑን አስርድቷል።

በዚህም ተግባሩ የዓለም ጤና ድርጅት መልካም ስምን፣ ገለልተኝነት እና ተዓማኒነት ክፉኛ መጉዳቱን ነው ያስገነዘበው።

ለሌሎች አርዓያ መሆን የሚገባው ዋና ዳይሬክተር በአንድ አባል አገር ላይ በደል በመፈፀም ከፍተኛ የስነ ምግባር ጥሰት መፈፀሙን አመልክቷል።

ይህ የዓለም ጤና ድርጅት የሰራተኞች ስነ ምግባር ደንብን የጣሰ የዋና ዳይሬተሩ ድርጊትን የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ በፍጥነት እንዲመረምር ጠይቋል።

ፅህፈት ቤቱ በመግለጫው ይህን የኢትዮጵያ ቅሬታን በተመለከተ ዶክተር ቴድሮስ በድርጅቱ ያላቸውን ሀላፊነት ለግል የፖለቲካ ዓላማው እየተጠቀመው መሆኑን በመግለፅ ለቦርዱ በይፋ ማስገባቱን ነው ያስታወቀው።

በመግለጫው የዓለም ጤና ድርጅት ይህን በአባል አገር ላይ እየተፈፀመ ያለን በደል ማስቆም አለበት ብሏል።

በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይም ሳይዘገይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.