Fana: At a Speed of Life!

ለመርሳት ችግር የሙዚቃ ህክምና 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙዚቃ ህክምና የማስታወስ ችግር ላለባቸው ሰዎች ተስማሚ ህክምና መሆኑን ጥናት አመላከተ፡፡

ከአዕምሮ ህመም ጋር የሚያያዘው ይሄው ችግር ሰዎች በዕለት ከዕለት ህይታቸው ማሰብ፣ ማመዛዘንና ማስታወስ እንዳይችሉ የሚያደርግ ነው፡፡

ይህ የጤና እክል በሂደት እያደገ የሚሄድ ሲሆን÷ በዕለት ከዕለት ህይወት ውስጥ ከሰዎች ጋር ለመግባባትና ለመቀራረብ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት እንደሚያሳየው የሙዚቃ ሕክምናን መጠቀም የማስታወስ ችግር ባለባቸው ሰዎች እና በተንከባካቢዎቻቸው መካከል ያለውን ማህበራዊ ግንኙነት ለማሻሻል ይረዳል።

ይህ አይነቱ ህክምና የታማሚዎችን ስሜት ለማስተካከል እና ደህንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው የተባለው።

የችግሩ ተጠቂ በሆኑ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናትም ÷ተጠቂዎች የሚወዱትን ሙዚቃ ከመረጡ በኋለ ሙዚቃውን እንዲያዳምጡ ተደርጓል፡፡

ለዚህ እንዲረዳም የህክምና ባለሙያዎቹ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡና የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን በማቆያ ማዕከል በማስገባት ለ12 ሳምንት ክትትል አድርገዋል።

ከቆይታቸው በኋላም መጠይቆችን በማዘጋጀት፣ ባህሪያቸውን በመገምገም እና ከተንከባካቢዎቻቸው መረጃ በመሰብሰብ ያሳዩትን ለውጥ ለመመዘን መሞከሩን የስነ ልቦና ሃኪም ዶክተር ቤታኒ ኩክ ተናግረዋል።

በዚህ ሂደትም ሰዎቹ ሙዚቃውን ከዳመጡ በኋላ በሙዚቃው ከመነቃቃት እና ከመዝናናት ባለፈ ከሙዚቃው ጋር ያሉ ትዝታዎችን እና ታሪኮችን ማስታወስ መቻላቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም ይታይባቸው የነበረው ድብርት መቀነሱንና የተሻለ መነቃቃት እንዲሁም ለነገሮች ትኩረት የመስጠት አቅማቸው በእጅጉ መጨመሩን  የጥናትቱ ውጤት  አመላክቷል።

የታየው ለውጥና መሻሻል አበረታች ቢሆንም ግን ጥናቱ የተደረገው በ12 ሳምንታት ሙከራ ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ ጥናትና ምርምሮች እንደሚያስፈልጉ ተጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈም የሙዚቃ ህክምናው ያመጣው መፍትሄ ዘላቂ ስለመሆን አለመሆኑ ተጨማሪ ጥናቶች ማድረግ ይገባል መባሉን ሜዲካል ኒውስ ቱደይ አስነብቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.