Fana: At a Speed of Life!

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በጋምቤላ ክልል በጎርፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች 15 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በጋምቤላ ክልል በጎርፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች 15 ሚሊየን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ።

የዓይነት ድጋፉን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የእርሻና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አስረክበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በስነ ስርዓቱ ላይ ፥ ድጋፉ በወሳኝ ወቅት ላይ የተደረገ በመሆኑ ለሕዝብ ያላችሁን ክብር አይተንበታል ብለዋል።

የጎርፍ አደጋው በክልሉ በአስር ወረዳዎች ከ187 ሺህ በላይ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልፀው ፥ ሚድሮክ ይህንን ድጋፍ ማድረጉ ትልቅ እርምጃና የአጋርነት ማሳያ እንደሆነ አስረድተዋል።

የክልሉ መንግስት የጎርፍ አደጋው ያደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ኢንቨስትመንት ግሩፑና ሌሎች አካላት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እርዳታ ከመስጠት በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ውጤታማ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የእርሻና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ከበደ በበኩላቸው ድርጅታቸው በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች 15 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 2ሺህ ኩንታል ዱቄት መለገሱን አመልክተዋል።

በቀጣይም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቁመው ፥ በዛሬው ዕለት እንደ ሀገር የበጎነት ቀን በሚከበርበት ሰዓት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን እንዳሉት ፥ በክልሉ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በአሁኑ ሰዓት በአስር ወረዳዎች ላይ ከ187 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልፀዋል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ፥ በቀጣይም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ መጠየቃቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.