Fana: At a Speed of Life!

በኮሮና ቫይረስ ስጋት ውስጥ ከመግባት ይልቅ የጤና ባለሙያዎችን ምክር በመተግበር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ አላስፈላጊ ስጋት ውስጥ ከመግባት ይልቅ የጤና ባለሙያዎችን ምክር በመተግበር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ሊያደርገው በሚገባው ጥንቃቄ ዙሪያ መልእክት አስተላልፈዋል።

አቶ ሽመልስ በመልእክታቸውም፥ ህብረተሰቡ ቫይረሱ ከአንዱ ወደ ሌላው በቀላሉ እንዳይተላለፍ ከእጅ ንክኪ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ደረቅ ሳል፣ የጉሮሮ ህመም፣ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ሙቀት (ትኩሳት) እና መሰል ምልክቶች ከታዩበት በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት ሊሄድ ይገባልም ብለዋል።

አቶ ሽመልስ አክለውም፥ በጤና ባለሙያዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መልእክቶችንና ምክሮችን መተግባር፣ እጅን በአግባቡ በሳሙና መታጠብ እና በተለመደው መንገድ ተቃቅፎ ሰላም ከመለዋወጥ መቆጠብ ይጠበቅብናልም ብለዋል።

በመንግስት፣ በጤና ባለሙያዎች፣ በህብረተሰቡ እና በሚመለከታቸው አካላት ትብብር
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በስኬት ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ተነሳሽነት መስራት ይገባልም ብለዋል።

አቶ ሽመልስ ለህብረተሰቡ ባስተላለፉት መልእክትም፥ ለበሽታው ተገቢ ያልሆነ ግምት በመስጠት ራስን ስጋት ውስጥ በመክተት ከመደበኛ ስራ መቅረት እንደሌለባቸው አስታውቀዋል።

ከስጋት ይልቅ በጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ ምክሮችን እና መልእክቶችን በመከታተል እና በመተግበር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.