Fana: At a Speed of Life!

የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ።

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።

በጉባዔው ላይ ተገኝተው የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ያቀረቡት ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ÷ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 88 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 60 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡

የኅዳሴ ግድብ በሁለት ዩኒት ኃይል ማመንጨት መቻሉ እና የግድቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት የ2014 ዓ.ም ወሳኝ ክንውኖች መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

እየታየ ላለው ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤቱ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸው÷ ተሳትፎው ሊጠናከር ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ፕሮጀክቱን በ70 ቢሊየን ብር ለማጠናቀቅ ታቅዶ የተጀመረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እስከ ሐምሌ 2014 ዓ.ም ብቻ የወጣው ገንዘብ 172 ቢሊየን ብር መድረሱን አስረድተዋል።

አጠቃላይ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅም ተጨማሪ 60 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ÷ተሳትፎው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር በበኩላቸው÷ በ2014 ብቻ በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያዎች 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ከኅብረተሰቡ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.