Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡትን መግለጫ ውድቅ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 4 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡትን መግለጫ ውድቅ አደረገ።

 

የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ከትናንት በስቲያ የህወሓትን ጠብ አጫሪነት እና ወረራ ወደ ጎን በመተው መንግስትን ለግጭቱ ተጠያቂ በማድረግ መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል።

ከዚህ ባለፈም የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን በመደገፍ፥ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡት መግለጫ ሃላፊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቋል።

መግለጫው ኮሚሽኑ ህወሓት የሰብአዊ ተኩስ አቁሙን በመጣስ ስለፈጸመው ጠብ አጫሪነት ምንም አለማለቱን በመጥቀስ፥ ኮሚሽኑ ለሰላምና ለደህንነት ስጋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመናገርም ሆነ የመወሰን ስልጣን እንደሌለው አንስቷል።

ይሁን እንጅ ኮሚሽኑ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ማቅረቡን በመጥቀስ፥ ይህ ድርጊቱ የኮሚሽኑን ሃላፊነት የጎደለው ባህሪ እንደሚያሳይ ገልጿል።

ይህም መንግስት የኮሚሽኑ እንቅስቃሴና ስራ ፖለቲካዊ ይዘት አለው በሚል የሚያነሳውን ሃሳብ ያረጋገጠ ሆኗልም ነው ያለው።

ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን የፖለቲካ ጫና ለማሳረፍ እየተጠቀመባቸው ነው ያለው መግለጫው ይህ አካሄዱም የኮሚሽኑን እውነተኛ ማንነት ያጋለጠ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።

የኮሚሽኑን መግለጫ ውድቅ ያደረገው ሚኒስቴሩ መንግስት የሰብአዊ መብቶችን በማክበር እና በማስከበር አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.