Fana: At a Speed of Life!

የጠላትን ሀገር የማፍረስ ፍላጎት በመመከታችን ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የልማት ውጥኖችን እውን እያደረገች ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠላቶቻችንን ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ፍላጎት በተቀናጀ ትግልና ተጋድሎ በመመከታችን ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የሆኑ የልማት ውጥኖችን እውን እያደረገች ነው ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “መከታ” በተሰኘው የመከላከያ ሠራዊት መጽሔት ላይ ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም 2013 እና 2014 ዓ.ም በአንድ በኩል ሀገራችን በርካታ ፈተናዎችንና የሕልውና አደጋዎችን የተጋፈጠችበት በሌላ በኩል በሕዝባችን፣ በመሪዎቻችን፣ በመከላከያና በፀጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ትግል ፈተናዎቹን በፅናት ያለፍንበትና በድል አድራጊነት የተሸጋገርንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም መባቻ ኢትዮጵያውያን ሰላም አግኝተው የሀገር ግንባታ ላይ ማተኮር መቻላቸው እንደ እግር እሳት የሚያንገበግበው ትህነግ የመንግሥትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ጥሶ ውጊያ መክፈቱን አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጅ በተቀዳጀነው ድል የተገኙትን ውጤቶች መቀልበስና ቀጣዩን የዕድገት ግስጋሴ መግታት እንደማይቻለውም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ትህነግ 250 ሺህ ተዋጊ ኃይል ይዞ ከ44 ሺህ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ተዋግቶ መፍረክረኩን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

ለስምንት ወራት በውጊያና አሰሳ ላይ ቆይቶ ከትግራይ የወጣው ኃይላችን መልሶ ባልተቋቋመበት ሁኔታ ከ500 ሺህ በላይ የትህነግ ተዋጊ ማዕበል ተረባርቦበት እንኳ አለመንበርከኩንም ነው የተናገሩት።

ትህነግ ሰሜን ሸዋ ደርሶ “ጦርነቱን ጨርሰነዋል” ብሎ ቢፎክርም የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በዓይኑ እንደዞረ በሠራዊት ክንድ መደቆሱን አውስተው፥ የቋመጠለትን ስልጣንም እንዳመረው መቅረቱን ነው የገለጹት፡፡

እኛ ወታደሮች ብንሆንም የሰላምን አማራጭ እናስቀድማለን ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፥ የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣልና ሕዝብን ለማጎሳቆል ያለመ ኃይል ውጊያ ከከፈተብን ግን በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሣራ መመከት የሚያስችል ቁመናና ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ሲሉም አስረድተዋል።

የውጪና የውስጥ ጠላቶች በቀጥታ ውጊያዎች፣ ሕዝብ ከሕዝብ በሚያጋጭ የሴራ ፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲና በስነ ልቦና ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ መክፈታቸውን ገልጸው፥ በተለያዩ ግንባሮች የተከፈቱ ውጊያዎችን ለመመከት ሠራዊቱ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

ሕዝቡ ለሠራዊቱ በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብና በተለይም በ“ሞራል” እያደረገ ያለውን አድንቀዋል።

የሕዝቡን ድጋፍና የሠራዊቱን የዓላማ ፅናት በማቀናጀት በሳል አመራር የሰጡ መሪዎች፣ የጦር አዛዦች፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች የጠላትን ከበባ በጣጥሰው አከርካሪያቸውን በመስበር ላጎናጸፉን ድል ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

ዓለም አቀፉ አሸባሪ አልሻባብ የመከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ ኃይሎች ባሳረፉበት ጠንካራ ምት ዳግም ኢትዮጵያን በማይተነኩስበት ደረጃ መቀጥቀጡን አውስተዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እንዳንሸጋገር አቅማቸው የፈቀደውን የማደናቀፍ ሙከራ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።

በአማራ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በአራቱም የወለጋ ዞኖች፣ በምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ጉጂ ሀገር ለማተራመስ መንቀሳቀሳቸውንም ነው ያወሱት።

አልሸባብ በምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ከሸኔና ከትህነግ ኃይሎች የተውጣጡ አሸባሪዎችን ወደ መሃል ሀገር ለጥፋት ተግባር መላኩን ጠቅሰው፥ ሁሉም የሴራ ድሮች በፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ክትትልና አመራር መምከናቸውን አስረድተዋል፡፡

2014 ዓ.ም የፈተና ጊዜና ፈተናዎቹንም በድል ተወጥተን ወደ 2015 የተሸጋገርንበት ዘመን ነው ብለዋል፡፡

የጠላቶቻችንን ሀገርን የማተራመስና የማፍረስ ፍላጎት በተቀናጀ ትግልና ተጋድሎ በመመከታችን ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የሆኑ የልማት ውጥኖችን እውን እያደረገች ትገኛለችም ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፡፡

በዘመናዊ ትጥቅና በሰው ኃይል አደረጃጀቱ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት መወጣት ወደ ሚችልበት ደረጃ የተሸጋገረው ሠራዊት፥ በቀጣይም ዝግጁነቱን ባልተቋረጠ ሁኔታ እንደሚያሳድግ አረጋግጠዋል።

አክለውም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣ ጠላትን እንደሚመክት ያረጋገጡት ፊልድ ማርሻ ብርሃኑ ጁላ፥ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የዕድገትና የኢትዮጵያ ከፍታ ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.