Fana: At a Speed of Life!

በ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 4 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የችግኝ ዝርያዎች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በ2014 ዓ.ም ከ34 ሚሊየን በላይ ህዝብ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሳትፏል ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ከዘመቻ አውጥቶ በመደበኛ ፕሮግራም ለማስኬድ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የደን መመናመን በኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በአካባቢ ላይ ያመጣውን ችግር መገንዘብ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው÷ የደን መመናመን በዋናነት ለተደጋጋሚ ድርቅ እያጋለጠን ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ለአፈር መሸርሸር፣ ለጎርፍ መጠቃት እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለመቻል እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
ተጋላጭነቱን ለመቀነስ የለማች፣ የበለጸገች እና ከተፈጥሮ ጋር የታረቀች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን የገለጹት ፕሮፌሰር ኢያሱ÷ 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል አበረታች ስኬት መመዝገቡን አመላክተዋል።
ከዚህ ውስጥ 47 በመቶ ደንና ቀርቀሀን እንደሚሸፍን፣ 52 በመቶው የሚሆነው ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የመኖ ዛፎችን ያካተተ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ሂደት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የችግኝ ዝርያዎች መተከላቸውንም ጠቁመዋል።
በመርሐ ግብሩ ጉድጓድ በማዘጋጀት፣ ችግኝ በማጓጓዝና በመትከል ለተሳተፈው ህዝብ ከፍተኛ አድናቆት አለን ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
መርሐ ግብሩን ለማስተባበር ከፍተኛ አመራሩ በተለይ የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ዓብይ እና ንዑሳን ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን እየመራ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
ስራውን ከተፋሰስ ልማቱ ጋር አስተሳስሮ ለመምራት እየተሞከረ መሆኑን ጠቅሰው÷ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ የተቀናጀ የህብረተሰብ ተፋሰስ ልማት ተብሎ ይወሰዳልም ነው ያሉት፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.