Fana: At a Speed of Life!

2014 ዓ.ም በሀገራችን ላይ የአሸባሪዎችና ዓለም አቀፍ ጫናዎች ቢበረቱበትም ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ነው- አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለፈው ዓመት በህዳሴው ግድብ ላይ ጭምር ዓለም አቀፍ ጫና የበረታበት እና አሸባሪው ህወሓት ከተባባሪዎቹ ጋር ሆኖ ሀገራችን ላይ ጫና ያሳደሩበት ጊዜ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን በአሸናፊነት ያለፍንበት ዓመት ነበር ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ፡፡

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም 2014 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይደረግ ዓለም አቀፍ ጫና የበረታበት እና አሸባሪው ህወሓት ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ጋር አብሮ ሀገራችን ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደሩበት ጊዜ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ጫናዎችን በአሸናፊነት ያለፉበት ዓመት ነው ብለዋል።

አዲሱን አመት ስንቀበል ካለፈው ዓመት በጎነትን፣ መረዳዳትንና መደጋገፍን በማስቀጠል እንዲሁም ለላቀ ብልፅግናና ከፍታ በመትጋት መሆን እንዳለበት በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም አቅመ ደካሞችን በመርዳት እና ማዕድ በማጋራት እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡

ሀገርና ሕዝብን ከጉዳት ለመከላከል ህይወት እየከፈሉ ላሉ ጀግኖች÷ ደጀን በመሆን፣ ክብርና ፍቅር በመስጠት ብሎም በአሸባሪዎች ጭካኔ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ አዲሱን ዓመት ልናከብር ይገባልም ነው ያሉት።

አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የድል፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.